ከ202 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና መሰረዙን ተከትሎ ተማሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ነው

ግንቦት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና መሰረዙ በተለዩ አካባቢዎች ተማሪዎች ተቃውሞ እንዲያነሱ እያደረጋቸው ሲሆን፣ መንግስት ለደረሰባቸው ኪሳራ ተገቢውን ካሳ እንዲሰጥ ይጠይቃሉ።

በምእራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ የሚገኙ ተማሪዎች ባካሄዱት ተቃውሞ ፣ “የፈተናው ወረቀት ለእኛም ይሰጠንና እንዘጋጅበት፣ ይህ ካልሆነ ፍትሃዊ ውድድር እንዳልተደረገ ይቆጠራል” የሚል ጥያቄ አንስተው ተቀባይነት ባለማግነቱ ፣ ተማሪዎቹ መፈክሮችን በማሰማት የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን ደብድበዋል። ተማሪዎቹ “የወያኔ መንግስት ስልጣን መልቀቅ አለበት፣ ወያኔ አይገዛንም፣ መሪያችን ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ነው፣ ወያኔ ኢትዮጵያን የመምራት አቅም የለውም፣የት/ት ጥራት መረጋገጥ አለበት፣ ወያኔ ይውደም፣የአማራ ህዝብ በተለያየ መለኩ በወያኔ ስርአት እየተጨቆነ ነው ፣ይህ ስርአት ይበቃዋል እና በቃ ” የሚሉ እና ሌሎችንም  መፎክሮች እያሰሙ ከት/ት ጽ/ቤት በመነሳት በየተቆማቱ ደንጋይ በመወርወር ወደ ብአዴን ጽ/ቤት፣አስተዳደር ጽ/ቤት እና ወደ ፖሊስ ጽ/ቤት ድንጋይ በመወርወር ላይ እንዳሉ  ከ30 በላይ የፖሊስ አባላት በሰልፈኛው ለይ  ጥይት ተኩሰው ለመበተን ሞክረዋል፡፡ ተማሪዎቹ በቁጣ በወሰዱት እርምጃ በርካታ የፖሊስ አባላትን እና ደጋፊዎችን በድንጋይና በዱላ አቁስለዋል፡፡

የአገር ሽማግሌወች “እንዴት በልጆቻችን ለይ ጥይት ትተኩሳላችው?” በማለት በፖሊሶች ላይ ወቀሳ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሽማግሌዎቹ ወጣቶችን ለማረጋጋት ሲጥሩ ታይቷል። ተቃውሞውን ተከትሎ 5 ያክል ተማሪዎች በመታሰራቸው ፣ ተማሪዎቹ ጓደኞቻቸው ካልተፈቱ ተቃውሞውን እንደሚቀጥሉበት አስጠንቅቀዋል።

በሃረር ከተማ የቀሃስ ተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውንምና  ፖሊስ ተቃውሞውን መበተኑን ወኪላችን ገልጿል። የ10ኛ ክፍል እና የ12ኛ ክፍል አገራቀፍ ፈተናን ለማዘጋጀት 202 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገዛሀኝ በግንቦት7 ታትሞ ለውጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረው ነበር።

መንግስት ፈተናውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም፣ የፈተናው መስጪያ ጊዜ ከኢድአል ፈጥር በአል ጋር መያያዙ በማህበራዊ ሚዲያ ትችት ካስነሳ በሁዋላ መንግስት በበአሉ ቀን ፈተና እንደማይኖር ገልጿል። ይሁን እንጅ ፈተናው በአጠቃላይ በበአሉ ሳምንት መደረጉ በሙስሊም ተማሪዎች ውጤት ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ተማሪዎች በድጋሜ ለመዘጋጀት ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል ፣ በድጋሜ ይሰረቃል በሚል በሙሉ ልብ ላይፈተኑ እንደሚችሉና በአጠቃላይ ውጤታቸውንም በጸጋ ለመቀበል እንደሚቸገሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በተለይ ከገጠር ወደ ከተማ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ የደሃ ልጆች መንግስት እስከፈተናው ቀን ድረስ ወጪያቸውን ሊሸፍንላቸው እንደሚገባ እየተናገሩ ነው።