ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሂሳብና ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ ህገወጥ ግዢ መፈጸሙን ጄኔራል ኦዲተር አስታወቀ

ግንቦት ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌዴራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ የ2007 በጀት አመት ኦዲት ካደረጋቸው 145 የመንግስት መ/ቤቶች መካከል 94 ያህሉ ከ 2 ቢሊየን ብር በላይ ሂሳባቸውን በወቅቱ ሳያወራርዱ የተገኙ ሲሆን ፣ 77 መ/ቤቶች ደግሞ ከ546 ሚሊየን ብር በላይ ከህግ ውጪ ግዥ ፈጽመው መገኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ዋና ኦዲተሩ በዛሬው እለት ለፖርላማ ባቀረቡት የ2007 በጀት አመት ሪፖርት 2 ቢሊዮን 78 ሚሊዮን 949 ሺ 440 ብር ከ60 ሳንቲም ያልተወራረደ ገንዘብ መኖሩን ገልጾ፣ ሂሳባቸውን ካላወራረዱት መካከል የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ 342 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር፣ ትምህርት ሚ/ር 315 ሚሊዮን 1 መቶ ሺ ብር፣ ምርጫ ቦርድ 172 ሚሊዮን 1 መቶ ሺ ብር፣ መከላከያ ሚ/ር 139 ሚሊዮን 2 ሺ ብር ይገኙበታል።
የግዥ አዋጅ ደንብና መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ ግዥ ፈጽመዋል በሚል በዋና ኦዲተር ሪፖርት ከቀረበባቸው ተቋማት መካከል ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 161 ነጥብ 3 ሚሊየን፣ አማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆ/ል 81 ሚሊየን፣ ደ/ማርቆስ የኒቨርሲቲ 45 ሚሊየን፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ 33 ሚሊየን፣ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዪት 26 ሚሊየን፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 25 ሚሊየን፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 20 ሚሊየን፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ 18 ሚሊየን፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 17 ሚሊየን፣ ትራንስፖርት ሚ/ር 15 ሚሊየን ብር ተጠቅሰዋል። በተጨማሪም 6 መ/ቤቶች ያለውል ሰነድ 22 ሚሊየን ብር ክፍያ ፈጽመው መገኘታቸውን ዋና ኦዲተሩ አጋልጦአል።