ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህጻናትና በእርግዝና ላይ የሚገኙ እናቶች ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸው ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች መቅረብ ያለበት ድጋፍ በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህጻናትና በእርግዝና ላይ የሚገኙ እናቶች ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የእርዳታ ተቋማት ገለጡ።

ተረጂዎችን ለመታደግ የሚደረገው ጥረት እስከቀጣዩ ወር ድረስ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት ካልተጀመረም በሃገሪቱ መጠነ-ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ተቋማቱ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የአለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ የሆኑት ጆን አይሊፍ ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ተጨማሪ እርዳታ ባለመገኘቱ ሳቢያ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ተረጂዎች ከአንድ ወር በኋላ የሚቀርብላቸው ድጋፍ እንደማይኖር ለሮይተርስ አስረድተዋል።

የህጻናቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ እንደሚገኝ የተናገሩት ሃላፊው በተለይ እድሚያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ እና በእርግዝናም ላይ ያሉ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች ልዩ ትኩረትን እንደሚሹ አስታውቀዋል።

ነዋሪነታቸ በአማራ ክልል ዋግ ህምራ ዞን የሆኑ ተረጂዎች በበኩላቸው የሚቅርብላቸው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ችግር ፈጥሮባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሃና መኮንን የተባለች የ30 አመት እናት አራት የቤተሰብ አባላት ቢኖራትም እርዳታ እያገኘች ያለችው ግን ለሁለት ቤተሰብ ብቻ እንደሆነ ለሮይተርስ ተናግራለች።

በአካባቢው የጤና መኮንን የሆነችው ፍሬህወት ዘሩ በበኩሏ በቂ የእርዳታ አቅርቦት ባለመኖሩ ሳቢያ በተለይ ህጻናት በምግብ እጥረት ሳቢያ የከፋ የአካልና የጤና ችግር እንደደረሰባቸው እንደሚገን አስረድታለች።

የኢትዮጵያ መንግስት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ መስጠት ያለበት ድጋፍ ቢዘገይም ለተረጂዎች በበቂ ሁኔታ ድጋፍ ይቀርባል ማለቱን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

ይሁንና በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ጆን ግራም አሁን ያለው የእርዳታ ክፍተት እንዴት እንደሚቀርፍ “አስጨናቂ” መሆኑን ገልጸዋል።

ከ 10 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ስጋትን ፈጥሮ የሚገነው ይኸው የድርቅ አደጋ በሃገሪቱ ታሪክ በአስከፊነቱ ሲከሰት በ50 አመት ውስጥ የመጀመሪያው መሆኑ ይነገራል።