ከ15 ዓመታት በኃላ የሥጋ ደዌ ሕመም አገረሸ

ሐምሌ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዓለም አቀፍ ደረጃ መጥፋቱ የሚነገርለት የሥጋ ደዌ ሕመም በአዲስ መልክ በኢትዮጽያ ማገርሸቱ አስደንጋጭ መሆኑን የኢትዮጽያ የቆዳና የአባላዘር በሽታዎች ሕክምና ማህበር በሂልተን ሆቴል ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ላይ ይፋ አደረገ፡፡
በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ መጥፋቱ የተረጋገጠው ከ15 ዓመታት በፊት መሆኑ የተነገረ ሲሆን ፣ በአሁኑ ወቅት ግን በኢትዮጵያ በዓመት ከ4ሺ በላይ አዳዲስ ሕሙማን መታየት መጀመራቸውና ከነዚህ ሕመምተኞች መካከል የሕጻናት ቁጥር
እያደገ መምጣቱ የዓለም ጤና ጥበቃ ተቋምን ጭምር እንዳሳሰበው ተመልክቶአል፡፡
በሽታው እድገት ሊያሳይ የቻለው በቂ ትኩረት ስለተነፈገውና የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭቱ አነስተኛ በመሆኑ ነው ሲሉ በመድረኩ ላይ የተገኙ ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡ ችግሩ በመላ ሀገሪቱ የሚታይ ቢሆንም በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች ሰፋ ብሎ እየታየ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሀገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎች ለበሽታው ሕክምና የሚሰጡ ቢሆኑም በበቂ ሁኔታ ሥራውን እያከናወነ ያለው የአለርት ሆስፒታል ብቻ መሆኑም ተጨማሪ ችግር ሆኖአል ተብሎአል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ እከተላለሁ ቢልም እንደሥጋ ደዌ ያሉ ሕመሞች ከመስፋፋታቸውና የሕዝብን ጤና ከማወካቸው በፊት ሊከላከል አለመቻሉ በመንግስት ደረጃ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል ተብሏል፡፡
የጊኒ ወርም በሽታም በኢትዮጵያ እንደገና መታየቱን ኢሳት በሰሞኑ ዘገባ አቅርቧል።