ከ100 በላይ የፓርላማ አባላት ባልተገኙበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸደቀ

ከ100 በላይ የፓርላማ አባላት ባልተገኙበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸደቀ
(ኢሳት ዜና የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ/ም)ኢትዮጵያውያን እና የውጭ አገር መንግስታት በእያቅጣጫው አፋኙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተቃወሙ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ዛሬ የተሰበሰው ፓርላማ፣ አዋጁን በ346 ድምጽ አጽድቆታል። በስብሰባው ላይ 106 የፓርላማ አባላት አልተገኙም። ከተገኙት መካከልም 88 የፓርላማ አባላት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። 7 አባላት ደግሞ ድምጸ ተቃውሞ አድርገዋል።
በህገ መንግስት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ) ላይ ህገ መንግስቱ የፓርላማ አባላቱ በተገኙበት በ2/3ኛ ድምጽ ይጸድቃል ቢልም፣ ከ547 የፓርላማ አባላት 364 አባላት መደገፍ ሲገባቸው የደገፉት ግን 346 ብቻ ሲሆኑ፣ አዋጁ 18 ድምጽ እየጎደለው በ2/3ኛ ድምጽ እንደተወሰነ ተደርጎ ቀርቧል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ኮማንድ ፖስቱ የቄሮንና የኦህዴድን እንቅስቃሴ ለመምታት እንቅስቃሴ እንደሚጀምር የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ባለፉት ወራት የቄሮን አደረጃጀት ለማወቅ ጥናቶች ሲሰሩ እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፣ እነዚህን መረጃዎች በመንተራስ በኦህዴድ አመራሮችና የቄሮ መሪዎች ናቸው በሚባሉት ላይ የእስር ዘመቻ ሊጀመር ይችላል። ህወሃት ኦህዴድን ከሁለት በመክፈል ትግሉን ለመቆጣጠር የነደፈውን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር እነዚሁ ምንጮች ይገልጻሉ። በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች የፌደራል ፖሊሶችና የአገዛዚ ወታደሮች እየተሰማሩ መምጣታቸውንም የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁን እንጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንደማያቆመው ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው። ህወሃት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ባሉ የመካከለኛ እና የታች አመራር አባላት ተቃውሞ የገጠመው በመሆኑ፣ በሚፈልገው መጠን ተቃውሞውን መቆጣጠር እንደማይችል የድርጅቱ አባላት ይገልጻሉ። የአዋጁ መጽደቅ እንደተሰማ በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ በተደረገው ተቃውሞ የአገዚ ወታደሮች ሁለት ሰዎችን መግደላቸው ታውቋል።
ራሱን ኮማንድ ፖስት ብሎ የሚጠራው ቡድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲጸድቅ በፓርላማ አባላቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥር ሰንብቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ውሳኔው አሳዛኝና ሃላፊነት የጎደለው ነው በማለት የአዋጁን መጽደቅ አውግዟል።
ባለፈው በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከባድ የሆኑ የሰብአዊ ጥሰቶችን መዝገበናል በማለት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተናገሩት የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ዋና ጸሃፊ፣ አዋጁ ከአለማቀፍ ህጎች ጋር የሚጣረሱ ድንጋጌዎችን ይዟል ብለዋል።
የዜና ድርጅቱ የፓርላማው ውሳኔ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለውን መከፋፈል ያሳያል ሲል ዘገባ አቅርቧል።