ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለመታደግ የሚደረገው ጥረት አነስተኛ መሆኑን እንዳሳሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ ገለጠ።
ለተረጂዎች እየቀረበ ያለው እርዳታ በማለቅ ላይ ቢሆንም ተተኪ የእርዳታ አቅርቦትን ለማድረስ እየተደረገ ያለው ጥረት ግን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ድርጅቱ በአፅንዖት አስታውቋል።
አለም አቀፍ የምግብ እርዳታን ወደሃገር ውስጥ ለማስገባት በትንሹ የሶስት ወር ጊዜን የሚወስድ ሲሆን እርዳታው ከውጭ እስከሚገባ ድረስ ለተረጂዎች ያለው የምግብ አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ሊያልቅ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድጋሚ ይፋ አድርጓል።
የምላሹ መዘግየትን ተከትሎም ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ከቀጣዩ ወር ጀምሮ የአቅርቦት ችግር ያጋጥማቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አለም አቀፍ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በበኩላቸው ጉዳትን እያደረሰ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ ወደረሃብ ሊቀየር ይችላል ሲሉ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
የመንግስት ባለስልጣናት ማሳሰቢያውን ቢያስተባብሉም ለተረጂዎች መቅረብ ያለበት ድጋፍ ግን በወቅቱ አለመቅረቡን እያሳሰበ መምጣቱን ገልጸዋል።
በስድስት ክልሎች በሚገኙ ከ180 ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በተለይ በህጻናት ላይ የከፋ ጉዳትን ያደርሳል ተብሎ ተሰግቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ለምግብ እርዳታ መጋለጣቸውንና ወደግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት የአካልና የጤና ጉዳት አጋጥሟቸው እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል።
በበልግ የዝናብ ወቅት መጣል የነበረበት ዝናብ በተገቢው መጠን ባለመገኘቱም ድርቁ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችልና የተረጂዎች ቁጥርም በቅርቡ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ድርጅቱ አክሎ አመልክቷል።
የድርቁ መባባስን ተከትሎ በሃገሪቱ በምግብ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መስተዋሉም ታውቋል።