ከ40 ሚሊዮን የሚበልጡ ታዳጊ ኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንደማያገኙ ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ህዳር 6 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ከ40 ሚሊዮን የሚበልጡ ታዳጊ ህጻናት ከመሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል አብዛኛውን የማያገኙ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ማክሰኞ ይፋ አደረገ።

መጠለያ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ትምህርት፣ መረጃ እንዲሁም የህጻናት ጥበቃ መሰረታዊ ፋላጎቶች ተብለው ቢቀመጡም በኢትዮጵያ 43 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት የዚህ ተጠቃሚ ሊሆኑ አለመቻላቸውን ድርጅቱ በደቡብ አፍሪካ ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቷል።

ከሰሃራ በታች ካሉ ከ20 አገራት መካከል ኢትዮጵያ ለታዳጊ ህጻናት መሰረታዊ ፍላጎትን ባለሟሟላት ግንባር ቀደም ሆና የተፈረጀች ሲሆን፣ ተጨማሪ 17.5 ሚሊዮን ህጻናት ከ1.25 የአሜሪካ ዶላር በታች እለታዊ ገቢ ያላቸው መሆኑንም የህጻናት መርጃ ድርጅቱ ገልጿል።

በሃገሪቱ ላሉ ታዳጊ ህጻናት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለሟሟላት ለአመታት ያህል የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆይም የተጠበቀው ለውጥ ሊመዘገብ አለመቻሉን ለመረዳት ተችሏል።

በተለይ የትምህርትና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለህጻናቱ ለማዳረስ አሁንም ድረስ ብዙ መሰራት ያለባቸው አበይት ጉዳዮች መኖራቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።

ባለፈው አመት በኢትዮጵያ በሚገኙ ስድስት ክልሎች ተከስቶ በነበረው የድርቅ አደጋ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ህጻናት ለምግብ እጥረት ተጋልጠው የነበረ ሲሆን፣ ችግሩ እስከ ቀጣዩ አመት ድረስ ቀጣይ እንደሚሆን ድርጅቱ በሪፖርቱ አስፍሯል።

ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠው ከሚገኙ ህጻናት መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት በምግብ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ የአካልና የጤና እክል ደርሶባቸው እንደሚገኝ የዕርዳታ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።

ባለፈው አመት በተከሰተው የድርቅ አደጋ አሁንም ድረስ ዕልባት ባለማግኘቱ ሳቢያ 9.7 ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያመለክታል።