ግንቦት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አምና ኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር እቃዎችን በመላክ ያገኘችው ገቢ ማሽቆልቆሉ ያስደነገጣቸው የመንግስት ባለስልጣናት በዚህ እና በመጪዎቹ አመታት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የማግኘት እቅድ ነድፈው ነበር። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ ተብሎ ተስፋ ከተጣለባቸው ምርቶች አንዱ ቆዳና ሌጦ ቢሆንም ፣ ባለፉት 9 ወራት የተገኘው ውጤት ከአምናው ጋር ሲተያይ ከ20 በመቶ በላይ አሽቆልቁሏል።
በእቅዱ መሰረት 129 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ ማግኘት የተቻለው 86.3 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ለውጤት መቀነስ የቀረቡት ምክንያቶች የጥራት ማነስ፣የሀይል መቆራረጥ ፣ የቆዳ እጥረት እንዲሁም በቂ የሆነ ባለሞያ እና አማካሪ ድርጅቶች አለመኖር መሆናቸው ተጠቅሷል።
መንግስት በተለያዩ ዘርፎች እንዳጋጠሙት የፓሊሲ ክሽፈቶች ሁሉ በቆዳውም ዘርፍ የታየው ክሽፈት የስርአቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውድቀት ማሳያ ነው በማለት የኢኮኖሚ ባለሞያው አቶ ኤድመን ተስፋዬ ተናግሯል፡፡ አቶ ኤድመን ከሀያ አምስት አመት የኢህአዴግ አገዛዝ በሁዋላም የሀገሪቷ የውጪ ንግድ ከቡና እና ቆዳ ባልተላቀቀበት በአሁኑ ወቅት የተሰማው ይህ ዜና የሀገሪቷ የውጪ ንግድ ሚዛን ምን ያህል እያሽቆለቆለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብሎአል፡፡
የውጭ ምንዛሬ ገቢው እያሽቆለቆለ ቢሆንም፣ አገሪቱ አሁንም ከአለም የግል ባንኮች ወይም በአጠቃላይ መጠሪያቸው ዩሮ ቦንድ ገንዘብ መበደሯን ቀጥላለች።
እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2015 ባሉት 5 ዓመታት ኢትዮጲያን ጨምሮ ዘጠኙ ከአፍሪካ ቀንድ በታች ያሉ አገራት ወደ 20 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ብድር መበደራቸውን ሰነዶች ያሳያሉ።
እነዚህ ሀገራት ሉአላዊነታቸውን በዋስትና በማስያዝ ለተበደሩት ብድር በየአመቱ ከነወለዱ 1.5 ቢሊየን ዶላር ይከፍላሉ፡፡ የኢህአዴግ መንግስት የሀገሪቱን ሉአላዊነት በማስያዝ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2013- 2015 ባሉት 2 አመታት ውስጥ ከግል ባንኮች 4 ቢሊዮን 100 ሚሊዮን ዶላር የተበደረ ሲሆን፣ ለእነዚህ ባንኮች የሚከፈለው ወለድ መጠን ፣ የብድሩ የመጠናቀቂያ ጊዜ መቃረብ በተለይም ከግንባታዎች መጓተት፣ ከውጭ ምንዛሬ ገቢ መቀነስ እንዲሁም እየጨመረ ከመጣው ሙስና ጋር ተያይዞ አገሪቱን አደጋ ውስጥ ሊጥላት ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
ለአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ባቡር ድርጅት ለአዋሽ ወልድያ ባቡርና ለአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ግንባታ 2 ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል።
ኢትዮ ቴልኮም ደግሞ የተለያዩ እቃዎችን ለመግዛት 1 ቢሊዮን 1 መቶ ሚሊዮን ብር ብድር ወስዷል። መብራት ሃይል ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሲበደር፣ ለእንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና ለስኳር ፕሮጀክቶች እና ለመሳሰሉት ደግሞ 1 ቢሊዮን ዶላር ብድር ተወስዷል።
እነዚህ የቅርብ ጊዜ ብድሮች አገሪቱ ከአለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ወይም ቻይናና ህንድን ከመሳሰሉ አገራት የተበደረቻቸውን ብድሮች አያካትቱም። ኢህአዴግ በስፋት ለሚበደረው ብድር በምክንያትነት የሚያቀርበው የመሰረተ ልማት ግንባታን ፣የውጪ ንግድ ተሳትፎን የሚያጠናክሩ የኢንደስትሪ ተቋማት ግንባታን እንዲሁም ፣የጤና እና የትምህርት ተቋማት የማስፋፋት ስራ የሚል ቢሆንም፣ የሀገሪቷ የውጪ እዳ እንደሚጨምረው ሁሉ መንግስታዊ ሌብነትም በዛው ልክ መጨመሩን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ አገሪቱ በከፍተኛ ወለድ የተበደረችው የውጪ ብድር የግለሰቦችን ኪስ እያደለበ ቢሆንም፣ ለህዝቡ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለማምጣቱ በአገሪቷ እየታየ እና ከእለት ተእለት እየከፋ ያለው ዘርፈ ብዙ ድህነት ማሳያ ነው በማለት እነዚህ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ያቀርባሉ።
በብድር ከተጀመሩት ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ልማት እቅዶች በሙስና ምክንያት ሳይሳኩ መቅረታቸው በቅርቡ ይፋ መሆኑ ይታወቃል።