ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መከሰቱን ነጋዴዎች ተናገሩ

ታኀሳስ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የንግድ ድርጅት ባለቤቶች ለኢሳት እንደገለጹት በአሁኑ ሰአት የተከሰተው የዶላር እጥረት ከምርጫ 97 በሁዋላ ከፍተኛው ነው። በአስመጭነትና ላኪነት ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ስራቸውን ለመስራት በማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ፋብሪካዎች የመለዋወጫ እቃዎችን ለመግዛት በመቸገራቸው እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ ተዳክሟል። በተለይ የግንባታ እንቅስቃሴው በእጅጉ መዳከሙን ነጋዴዎች ይገልጻሉ።
በአገሪቱ የተፈጠረውን ከፍተኛ ድርቅ ለማቋቋም መንግስት በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የእርዳታ እህል ለመግዛት ቢችልም፣ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠው ድጋፍ በመቀነሱ ተጨማሪ የእርዳታ እህል ለመግዛት አቅም አጥሮታል። ከዚህ ቀደም የተከሰተውን የዶላር እጥረት ለመቋቋም መንግስት ከአለማቀፍ የግል አበዳሪ ድርጅቶች 1 ቢሊዮን ዶላር ቢበደርም ፣ ሁለተኛው ዙር ብድር እስካሁን አለመለቀቁ ችግሩን አባብሶታል ሲሉ ምንጮች ይገልጻሉ።