ከፍተኛ ወጪ የወጣበትና ትናንት ሚያዚያ 22 ቀን 2009 ዓ ም በጎንደር የተከፈተው 7ኛው የከተሞች ፎረም እንደተጠበቀው ሊደምቅ አለመቻሉ ተገለጸ።

ሚያዝያ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህወኃት በዓሉን በልዩ ድምቀት ለማክበር በማሰብ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ግብረ ሀይል አቋቁሞ በርካታ የሰው ሀይል በመመደብና እና ከፍተኛ ገንዘብበማፍሠስ በዓሉ ርብርብ ቢያደርግም፣ በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የታሰበውን ያህል ውጤት ማግኘት ሳይቻል መቅረቱ ተመልክቷል።
በጎንደር መከበር በጀመረው በዚህ በዓል ተይዞ የነበረው ዕቅድ ህብረተሰቡ በነቂስ ወደ አደባባይ ወጥቶ በዓሉን እንዲያክብርና እንግዶችን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ነበር።
ይሕ እንዲሆንም በዓሉ ከመድረሱ በፊት አንስቶ ሰፊና ተከታታይ የማስተዋወቅ ሥራ ቢሰራም ፤በመንግስት አበል ተከፍሏቸው ከተገኙት ውጭ በመክፈቻው ሥነ ስርዓት ላይ የተገኝየህብረተሰብ ክፍል እንደሌለ በፍራው የተገኙት ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
በበዓሉ ላይ አምረው እንዲገኙ በማለት ለሴት የብአዴን አባላት 500 ብር ለፀጉር መሰሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ሁሉም የአገር ባህል ልብስ ለብሰው እንዲገኙ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
ለወንዶቹ ደግሞ አረንጏዴ ቢጫ እና ቀይ ቲሸርት የተዘጋጀላቸው ሲሆን፤ አልባሳት የተዘጋጀላቸው እነዚህ 300 ወጣቶች በቀን 250 ብር አበል እየተከፈላቸው ዝግጅቱ እስኪያልቅ ድረስየሚቆዩ ናቸው።
እንደ ምንጮች ገለጻ እነዚህ ታዳጊ ወጣቶች በአብዛኛው ህፃናት ሊባሉ የሚችሉ ሲሆኑ፤ ከየሰፈሩ አውጣጥተው የስበስቧቸው ናቸው።
በበዓሉ መክፈቻ ላይ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የፓርላማው አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ቢገኙም ፤ቢያንስ 15 ሺህ እንግዳ ይገኝበታል ተብሎ በተጠበቀው የበዓሉ መክፈቻ ከጥቂቶች ውጪ የታሰበውን ያህል ሰው ሊገኝበት አለመቻሉና የተቀዛቀዘ በመሆኑ፤ በእንግዶቹ ፊት ሳይቀር መደናገጥ ይነበብ እንደነበር ተመልክቷል።
የታሰበውን ያህል እንግዳ ያልመጣው የአካባቢው ጸጥታ አሁንም በአደጋ የተሞላ በመሆኑ ነው ሲሉ የዜናው ምንጮች አስተያዬታቸውን አስቀምጠዋል።