ኢሳት (ነሃሴ 23 ፥ 2008)
ህወሃት በአማራ ክልል እየተካሄደው ባለው ህዝባዊ ንቅናቄ በድንጋጤ ላይ የሚገኘው የህወሃት አገዛዝ፣ በጎንደር፣ ጎጃም፣ አዊ ዞኖች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማስቆም እንዲያግዙ ከ2ሺ በላይ የአጋዚ ጦር አባላትን ከአዲስ አበባ ትናንት ዕሁድ ወደ አማራ ክልል ማንቀሳቀሱ ተገለጸ።
በአማራ ክልል በጎጃምና ጎንደር የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ፣ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ የተረዳው የህወሃት አገዛዝ፣ ተቃውሞን በሃይል ለማስቆም መደበኛ ወታደርና የአጋዚ ገዳይ ቡድን በከተሞች አሰማርቶ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በመግደልና በማስፈራራት ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ለመቀልበስ እንዳቀደ ከስፍራው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ተቃውሞ በሚደረግባቸው ከተሞች የሰልፉ አስተባባሪ ናቸው የተባሉትን ወጣቶችን ለመያዝና ተቃውሞውን ለማስቆም ጥረት እንደሚያደርግ ከአማራ ክልል የኢሳት ምንጮት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአጋዚ ወታደሮች ወደ አማራ ክልል ገብተው የክልሉን ወጣቶች በአልሞ ተኳሽ መሳሪያ ከመጨረሳቸው በፊት፣ ህዝቡ ከየአካባቢው በነቂስ በመውጣት መንገድ በመዝጋት ጉዟቸውን እንዲያስተጓጉል ጥሪ ተደርጓል።
በብዓዴን አባላት ላይ ጥርጣሬ እያየለ የመጣው ህወሃት፣ በአማራ ክልል የኖሩ የህወሃት አባላት የሆኑ ሲቪል የለበሱ ሰላዮችን በማሰማራት ሰልፉን ያስተባብራሉ የተባሉትን ወጣቶችን እየለዩ እንዲሰጡ ማድረጋቸው ተነግሯል። በእንጅባራና ዳንግላ ከተሞች የህወሃት አባላትና ሰላዮች ሰላማዊ ተቃውሞ ያሰሙ ሰዎች ላይ በመተኮስ የሰው ህይወት እንዳጠፉና እንዳቆሰሉ ከስፍራ የደረሰን ዜና የመለክታል።