ሰኔ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኡስታዝ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱት 18 የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት በሙሉ ጥፋተኞች ሲባሉ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤት ለሃምሌ 27 ቀጠሮ ሰጠ።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛው ወንጀል ችሎት በ አቶ አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ፣ ካሚል ሸምሱ፣ በድሩ ሁሴን፣ ሼህ መከተ ሙሄ መኮንን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሀመድ አባተ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ አቡበከር አለሙ፣ ሙኒር ሁሴን፣ ሼህ ሰኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም፣ ካሊድ ኢብራሂም በተከሰሱባቸው በፀረ ሽብር ህጉ ጥፋተኞች ያላቸው ሲሆን፣ ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ኡመር እና የሱፍ ጌታቸው በፀረ ሽብር ህጉ አንቀፅ ሰባት መሰረት ጥፋተኛ ተብለዋል።
ተከሳሾች በጸረ ሽብር ህጉ መሰረት ከፍተኛው የእስር ጣራ የሚጠብቃቸው ሲሆን፣ የመጨረሻውን ፍርድም ሀምሌ 27 ይሰማሉ።
ፍርድ ቤት የመጨረሻውን ውሳኔ ያራዘመው ከኦባማ ጉብኝት ጋር በተያያዘ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃውሞ ሊያስነሳ ይችላል በሚል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።