ኢሳት (ሚያዚያ 24 ፥ 2009)
በኦሮሚያ ክልል ወርቅ ለማውጣት በዝግጅት ላይ የሚገኘው የብሪታኒያ ከፊ ሚነራል ኩባንያ ከአመታት በፊት በክልሉ አድርሷል በተባለ የአካባቢ ተፅዕኖ የ12 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ጉዳት ጥያቄ ቀረበበት።
ኩባንያው በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ቱሉ ቆቢ በተባለ ስፍራ ወርቅ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ሲሆን፣ ይህንን ፕሮጄክት ከመረከቡ በፊት በአካባቢው በተመሳሳይ እንቅስቃሴ በቆየበት ከ1998 እስከ 2006 አም በስፍራው አካባቢያዊ ጉዳት አድርሷል ተብሎ በክልሉ መንግስት ክስ እንደተመሰረተበት ታውቋል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የኦሮሚያ የይግባኝ ፍርድ ቤት በይግባኝ የቀረበውን ጥያቄ በመመልከት የካሳ ጉዳቱ 600ሺ የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን በቅርቡ ውሳኔ ማስተላለፉን ኩባንያው ማክሰኞ ለአባላቱ ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል።
የይግባኝ ፍርድ ቤቱ ኩባንያው የ600ሺ ዶላር የጉዳት ካሳ እንዲከፈል ቢወስንም የማዕድን ኩባንያው ጉዳዩን በተመለከተ በድጋሚ ይግባኝ ማቅረቡን አክሎ ገልጿል።
የኦሮሚያ የይግባኝ ፍርድ ቤት በከፊ ሚነራል የማዕድን ተቋም ላይ ያስተላለፈው ይኸው ብይን በአክስዮን አባላት ዘንድ ስጋት ማሳደሩም ታውቋል።
መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው ኩባንያ የኩሉ ቆቢ ፕሮጄክትን ከመረከቡ በፊት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1998 እስከ 2006 አም ድረስ ተመሳሳይ የማዕድን ማውጣት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይሁንና ኩባንያው ሲያካሄድ የቆየው ይኸው እንቅስቃሴ አካባቢያዊ ጉዳት አድርሷል የተባለ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከሶስት አመት በፊት ክስ መመስረቱን ለመረዳት ተችሏል።
የክልሉ መንግስት ለደረሰው ጉዳት የ120 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ቢጠይቅም ፍርድ ቤት የቀረበው የካሳ ጥያቄ በበቂ ማስረጃ የተደገፉ አይደለም በሚል የካሳ ክፍያው 600 ሺ ዶላር ብቻ እንዲሆነ ወስኗል።
ከፊ ሚነራልስ በቱሉ ቆቢ የወርቅ ማውጣት ስራውን ለመጀመር በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ከመንግስት ጋር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ኩባንያው በአካባቢ ያለን ወርቅ በብቸኝነት ለማውጣት ለ20 አመት የሚቆይ ውል እንደተሰጠውም ታውቋል።
በድጋሚ በይግባኝ ያቀረበው የፍርድ ሂደት በቀጣዩ ሁለት አመታት ውስጥ መታየት እንደሚጀምርም ኩባንያው በድረ-ገጹ ካሰፈረው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በአካባቢው ለረጅም አመታት የሞከሩ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንዲነሱ ቢገልፅም የክልሉ መንግስት ሆነ ኩባንያው ምን ያህል ሰዎች ከይዞታቸው እንደሚነሱ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።