ኢሳት (ሚያዚያ 30 ፥ 2009)
በኦሮሚያ ክልል የወርቅ ማውጣት ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኘው ከፊ ሚነራል ኩባንያ በቱሉ ቆቢ ፕሮጄክት የሚወጣውን የወርቅ ሃብት የሚያስተዳደር አካል ከመንግስት ጋር ማቋቁሙን ሰኞ አስታወቀ።
በአካባቢው የሚወጣውን ከፍተኛ የወርቅ ሃብት ለማስተዳደር በሁለቱ ወገኖች በተደረሰ አዲስ ስምምነት መንግስት 25 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪው 75 በመቶ ደግሞ የከፊ ሚነራል እንዲሆን ተወስኗል። መንግስት 25 በመቶ ድርሻን ለመያዝ 20 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ለኢንቨስትመንት ለመመደብ ስምምነት መደረሱ ታዉቋል።
የቀረው አምስት በመቶ ድርጃ ደግሞ መንግስት ምንም አይነት የፕሮጄክት ኢንቨስትመንት ሳያደርግ የሚኖረው ድርሻ መሆኑን ከፊ ሚነራል በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ ስራው ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ይኸው የቱሉ ቆቢ ፕሮጄክት በአጠቃላይ 15.4 ሜትሪክ ቶን የወርቅ ክምችት እንዳለው ታውቋል። መንግስትና ከፊ ሚነራል በቱሉ ቆቢ ፕሮጄክት ላይ ድርሻን ለመካፈል ስምምነት ቢደርሱም በፕሮጄክቱ አቅራቢያ ኩባንያው በሊዝ የተረከበው የወርቅ ማውጫ ቦታ ባለቤትነቱ ሙሉ ለሙሉ ለእሱ መሆኑን ገልጿል።
የወርቅ ማውጣት ስራውን ለመጀመር ነዋሪዎች ከቀያቸው እንዲነሱ እየተጠባበቀ የሚገኘው ኩባንያው የወርቅ ፕሮጄክቱን ለማልማት ከመንግስት የ20 አመት ፈቃድ ማግኘቱ ተመልክቷል።
መንግስትና ኩባንያው በፕሮጄክቱ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ዝግጅት እያካሄዱ ቢሆንም፣ ሁለቱ ወገኖች ምን ያህል ሰው ሊፈናቀል እንደሚችል የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም። በምዕራብ ወለጋ አካባቢ የሚገኘው የቱሉ ቆቢ የወርቅ ልማት ፕሮጄክት ስራውን በጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የወርቅ ማውጫ ስፍራን በሊዝ መያዙን ቢገልፅም በዚሁ ስፍራ ምን ያህል የወርቅ ሃብት እንዳለና እንደሚለማ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ኩባንያው ወደ ስራ እንደሚገባ ማስታወቁን ተከትሎ የባለአክሲዮኖች ድርሻ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኩባንያው ቱሉ ቆቢ ፕሮጄክትን ከመረከቡ በፊት በሌላ ተመሳሳይ ስራ ተሰማርቶ በአካባቢ ላይ ጉዳትን አስከትሏል በሚል የ12 ሚሊዮን የካሳ ጥያቄ ለፍርድ ቤት አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁንና የክልሉ ፍርድ ቤት የካሳ ጥያቄው በአግባቡ የቀረበ አይደለም በማለት የ12 ሚሊዮን የካሳ ጥያቄውን በማሳነስ 600 ሺ ዶላር ብቻ እንዲከፈል በቅርቡ ውሳኔን ሰጥቷል። ከፊ ሚኔራል ኩባንያ በበኩሉ የ600ሺ ዶላሩን የካሳ ክፍያ በመቃወም ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰደው ሲሆን፣ አቤቱታው በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ውስጥ መታየት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።