ሐምሌ ፲፪ ( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከግብር ጋር በተያያዘ የተጀመረው አድማ ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎ መዋሉን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች አመልክተዋል። አድማው አድማሱን እያሰፋ በመምጣት ላይ ሲሆን፣ የአገዛዙ ካድሬዎች ነጋዴውን ማህበረሰብ ከተቻለ በማግባባት ካልተቻለም በማስፈራራት አድማውን እንዲያቆም ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው።
አምቦ እንደ ሰሞኑ ሁሉ ዛሬም ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ወታደሮች ተከባ ውላለች። ወታደሮቹ በመኪኖች ላይ ተጭነው በአውራ ጎዳናዎች ላይ እየተመላለሱ ቅኝት ያደርጋሉ። ካደሬዎች ደግሞ ወደ ነጋዴዎች ቤት በመሄድ ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ለማግባባትና ለማስፈራራት ይሞክራሉ። እስካሁን ባለው መረጃ አምቦ ለሶስት ቀናት የተጠራውን አድማ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያዋ ከተማ ሆናለች።
በወሊሶ ደግሞ የአገዛዙ ካድሬዎች ነጋዴዎችን ሰብስበው አድማውን እንዲያቆሙ እና ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡ ተማጽነዋል። በሰብሰባው ነጋዴዎቹ ብሶታቸውን አሰምተዋል። ከሰአት በሁዋላ፣ መጠነኛ ቁጥር ያላቸው የንግድ ድርጅቶችና አንዳንድ ባጃጆች ስራ ጀምረዋል። ይሁን እንጅ የከተማው ነጋዴ አሁንም ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ አልተመለሰም።
አድማውን ዛሬ ረቡዕ ከተቀላቀሉት መካከል ነቀምት አንዱ ነው። በነቀምት አድማው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ በከተማውም ሆነ ከተማውን አቋርጦ በሚያልፉ መንገዶች ላይ ተሽከርካሪዎች አይታዩም። በዚህ ከተማ ከሌሎች በተለየ የወረዳው ካድሬዎች የንግድ ድርጅቶችን እየዞሩ አሽገዋል። ጊንቢ፣ ጊንጪ፣ ደንቢዶሎ፣ አርጆ፣ ወለታ፣ እና በአርሲ አንዳንድ ከተሞችም እንዲሁ አድማዎች በመደረግ ላይ ናቸው።
በጊንጪ አንድ መኪና መቃጠሉንም መረጃዎች አመልክተዋል።