ከግማሽ ቢሊዮን በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የጎንደር ከተማ ውሃ ፕሮጀክት በተመረቀ በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት አቆመ።
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 03 ቀን 2010 ዓ/ም) ለዘመናት በከፍተኛ የውሃ እጥረት ችግር ተጠቂ ከሆኑት የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው የጎንደር ከተማን የውሃ ችግር ከ44 በመቶ ወደ መቶ በመቶ ከፍ ያደርገዋል፣ በዘላቂነትም የከተማዋን የውሃ ችግር ይፈታል የተባለለት የውሃ ፕሮጀክት በተመረቀ በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት በማቆሙም፣ ህዝቡ ለከፍተኛ ችግር መዳረጉ እና ከ561 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ባክኖ መቀረቱ ተዘግቧል።
ፕሮጀክቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የውሃና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በተገኙበት ህዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድርና በመስተዳደሩ ወጪ ከ561 ሚሊዮን ብር በላይ የፈሰሰበት የውሃ ፕሮጀክት ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ዋስትና አለው ተብሎ ታስቦ የተሰራ ነው ተብሎ ነበር። አዲሱ ፕሮጀክት ስምንት ጥልቅ ጉድጓዶች ሲኖሩት፣ በሰከንድ እስከ 240 ሊትር፣ በቀን ደግሞ እስከ 17 ሽህ ሜትር ኩብ ውሃ እንደሚያመነጭና፣ ከአንገርብ የውሃ ማመንጫ ጋር ተዳምሮ በቀን እስከ 27 ሽህ ሜትር ኩብ ውሃ ያቀርባል ተብሎ ዲዛይን ተደርጎ መሰራቱ ይታወቃል። ይሁንና ጉድጓዶቹ በተባለላቸው መጠን የተጠበቀውን ያህል ውሃ ማመንጨት ሳይችሉ አገልግሎት መስጠት በማቆማቸው፣ የከተማዋ ነዋሪዎች በውሃ ማጣት ከመቸገራቸው በተጨማሪ ተጨማሪ ወጭዎችን ለማውጣት ተገደዋል።
ኢሳት ከወራት በፊት የውሃ ጉድጓዶች መድረቃቸውን መረጃ ደርሶ ሲከታተለው ቆይቷል። በግንባታው ላይ ከፍተኛ ሙስና መፈጸሙንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ችግሩን አስመልክቶ የጎንደር ከተማ ውሃ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ብዙ ገንዘብ ወጪ ወጥቶበት የተገነባው ፕሮጀክት የተጠበቀውን ያህል አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ በግንባታ ፕሮጀክቱ ላይ የተሳተፉ በሙሉ ተጠያቂዎች ናቸው ብለዋል።
ታሪካዊቷን የጎንደር ከተማን ጨምሮ በመዲናዋ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ መቀሌ፣ አሰላ፣ በመሳሳሉት ታላላቅና አነስተኛ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባሱ በነዋሪዎች ሕይወት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው።