ከጋንቤላ ታግተው ከተወሰዱት ሕጻናት የስድሳ ስምንቱ አድራሻ እስካሁን ድረስ  አልታወቀም

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- መነሻቸውን ከደቡብ ሱዳን ያደርጉ የሙርሌ ጎሳ አባላት ድንበር ተሻገረው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በጋንቤላ ክልል ውስጥ ጥቃት መሰንዘራቸው ይታወሳል። በወቅቱ የሙርሌ ታጣቂዎች መኖሪያ መንደሮች በእሳት አቃጥለዋል፣ የጅምላ ግያዎችን ጨምሮ ሕጻናትና ታዳጊዎች አግተው ወስደዋል። በወቅቱ ታግተው ከተወሰዱት ሕጻናቶች ውስጥ የተወሰኑት የተመለሱ ቢሆንም እስካሁን ድረስም ያሉበት አድራሻ የማይታ ወቁና ወደ አገራቸው ተመልሰው ከወላጆቻቸው ጋር መገናኘት ያልቻሉ 68 ሕጻናቶች መኖራቸው በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት አስታወቁ።

እነዚህን የታገቱ ሕጻናት ለማስመለስ  የሁለቱም አገራት ባለስልጣናት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት ወ/ሮ አኜስ ካላማርድ አሳስበዋል። ”የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ግጭቶች እንዳይከሰቱ እና እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች ዳግም እንዳያገረሹ ወሳኝ የሆኑ ተግባራዊ ስራዎችን መከወን አለባቸው” ሲሉ ኤክስፐርቷ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ከጋንቤላ ክልል የሙርሌ ጎሳ አባላት 13 የአኝዋክ መንደሮች ላይ ጥቃት ያደረሱ ሲሆን ጥቃቱን ተከትሎ 200 ንጹሃን ዜጎች በግፍ ተገለዋል። ከ150 በላይ ሕጻናትና ታዳጊዎች ታግተው ተወስደዋል። ታግተው ከተወሰዱት ውስጥ ቁጥራቸው ከ90 የሚሆኑ ሕጻናት በሁለቱ አገራት የጋራ ስምምነት ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደገዋል። በአሁኑ ወቅት ግን የማስመለስ ሒደቱ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድርጅት አስታውቋል። የሁለቱም አገራት ባለስልጣናት የቀሩትን ሕጻናት ወደ ቤተሰቦቻቸው ለማስመለስ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደላባቸው ኤክስፐርቷ አጽኖት ሰጥተው ማሳሰባቸውን ራዲዮ ታማጁል ዘግቧል።