ከጋምቤላ ጭፍጨፋ በስተጀርባ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ሳይኖሩበት አይቀርም ተባለ

ኢሳት (ሚያዚያ 14 ፥ 2008)

ባለፈው ሳምንት በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ የሙርሌ ጎሳ አባላት በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ግድያ፣ በሳልባ ኪርና በሪክ ማቻር መካከል ያለው የስልጣን ፍትጊያ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል አንድ አለም አቀፍ ጋዜጣ ዘገበ።

በኑዌር ብሄረሰብ ላይ ጥቃት ያደረሱት የሙርሌ ብሄረሰብ አባላት በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ መሆናቸውና በዲንቃ ጎሳ አባላት መታጀባቸው የሪክ ማቻር ጎሳ አባላት በአንድ በኩል የሳልባ ኪር ጎሳ አባላት በሌላ በኩል አካባቢውን በመሳሪያ ሲያጥለቀልቁ እንደቆዩ አመላካች ሊሆን እንደሚችል አትላንቲክ ካውንስል የተባለው ጋዜጣ በትናንትናው እትሙ ዘግቧል። ከዚህ የጦር መሳሪያ ዝውውርም የሙርሌ ጎሳ አባላት ተጠቃሚ ሳይሆኑም እንዳልቀረ ጋዜጣው ባወጣው ዘገባ አክሎ አስነብቧል።

ሰሞኑን የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አወሳስቦታል ያለው አትላንቲክ ካውንስል ጋዜጣ፣ ከሶስት ወር በፊት በአኙዋክና በኑዌር ጎሳዎች መካክል ግጭት ተከስቶ በርካታ ሰዎች ለሞት እና ለመቁሰል እንዲሁም ንብረት መውደም እንዳስከተለ ጋዜጣው ትንታኔ ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም እኙዋኮች በደርግ ጊዜ ማለትም እኤአ በ1980ዎቹ ጀምሮ በአካባቢው ከሰፈሩት ከደገኞች ጋር አልፎ አልፎ ግጭት ይገቡ እንደነበረ ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።

በጋምቤላ ክልል መንግስት በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት መካከለም በተለያዩ ጊዜያት ቅራኔዎች እንደነበሩ የተነተነው አትላንቲክ ካውንስል፣ በአካባቢው ጸጥታ በማስፈን ሂደትም ደገኞቹ ወታደራዊ መሪዎች ውሳኔ ሰጪ በመሆን የክልሉን ስልጣን ጠቅለው ወስደዋል ብሏል። እኤአ በ 2003 ዓም የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አኙዋክ ነዋሪዎችን ከገደሉ በኋላ በፌዴራል በክልሉ መንግስታት መካከል አለመተማመን በእጅጉ ሰፍኖ እንደቆየ ጋዜጣው በዘገባው አትቷል።

ይህ ሁሉ ተደማምሮ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደተገለሉ አይነት ስሜት ሊፈጥርባቸው እንደሚችልና ከደቡብ ሱዳን ጎሳዎች ሌላ ጥቃት ሊደርስባቸው እንደማይችል ምንም ዓይነት ዋስትና እንደማይሰማቸው ጋዜጣው አብራርቷል።