ኢሳት (ግንቦት 19 ፥ 2008)
ባለፈው ወር በጋምቤላ ክልል በሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የተፈጸመው ጥቃት ወደ 2ሺ በሚሆኑ ታጣቂዎች መፈጸሙንና በድርድር ያልተለቀቁ ህጻናት ጉዳይ አነጋጋሪ ሆነ መቀጠሉን አልጀዚራ የቴለቪዥን ጣቢያ አርብ ዘገበ።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ከጎሳ አባላቱ ተወካዮች ጋር ሲያካሄድ የቆየውን ድርድር ተከትሎ ወደ 53 የሚጠጉ ህጻናት የተለቀቁ ሲሆን የተቀሩ ህጻናት ህልውና ግን ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት መፍጠሩን የቴለቪዥን ጣቢያው ከነዋሪዎቹ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ በማቅረብ አስነብቧል።
ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት ወደ ሁለት ሺ በሚሆኑ የታጠቁ ሃይሎች መፈጸሙንና ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ ለአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄ ሆኖ መቅረቱን አልጀዚራ ዘግቧል።
ኤኬ-47 የሚል መሳሪያን አንግበው ነበር የተባሉት ታጣቂዎች የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሰራዊት መለያን አድርገው እንደነበር ቢገልጹም የሃገሪቱ መንግስት ጉዳዩን አስተባብሏል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ዳግም ወደ ደቡብ ሱዳን በመግባት በድርድር ያልተፈቱ ህጻናትን ለመፈለግ ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት በበኩሉ ከጎሳው ተወካዮች ጋር በተካሄደው ድርድር ወደ 53 ህጻናት መለቀቃቸውን አስታውቆ፣ ድርድሩ በምን ጉዳዮች ዙሪያ እንደተካሄደ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።
ድርድሩ ይቋረጥ አይቋረጥ በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰጠ መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የተቀሩ ህጻናት ጉዳይ ግን አስቸጋሪ እና መነጋገሪያ ሆኖ መገኘቱን አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በዘገባው አስፍሯል።
የጋምቤላ ክልልል ፕሬዚዳንት ጋትሉአክ ቱት በበኩላቸው ታፍነው የተወሰዱት ህጻናት ለሌላ ጎሳዎች ተሽጠዋል የሚል መረጃ እየደረሳቸው መሆኑን ሱዳን ትሪቢዮን ጋዜጣ ገልጿል።
ለሌላ ጎሳዎች ተሸጠዋል አልያም በከብቶች ተቀይረዋል የተባሉ ህጻናት ለማስመለስ መንግስት የተቻለውን ጥረት ሁሉ እንደሚያደርግ ሃላፊው አስታውቀዋል።
ታፍነው የተወሰዱ ህጻናት ቁጥርን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ቢሰራጩም ቢቢሲ ከቀናት በፊት ታፈነው የተወሰዱ ህጻናት 149 መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስታት ታፍነው የተወሰዱ ህጻናት ለመታደግ የተቻላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ሃሙስ ማሳሰቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከቀናት በፊት ቦማ ተብሎ ወደሚጠራት የደቡብ ግዛት ቢገቡም የግዛቲቱ ሃላፊዎች ወታደሮቹ ሊያደርጉት ላሰቡት ወታደራዊ ዘመቻ ፈቃድ አለመስጠታቸውን የደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።