(ሐምሌ -5/2009)በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ስር የተቋቋመው አጥኚ ቡድን ውላቸው እንዲቋረጥ ካደረጋቸው በጋምቤላ እርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩት ባላሃብቶች ውስጥ ቅሬታ ካቀረቡት 98 በመቶ ወደ ስራ መወሰኑ ነው የተገለጸው። በጋምቤላ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን እንቅስቃሴ ለማጥናት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ስር የተቋቋመው አጥኚ ቡድን ለተራዘመ ወራት ጥናት በማካሄድ የተሰጣቸውን የባንክ ብድር ለሌላ ተግባር ያዋሉ፣ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ያልገቡ ፣መሬቱን ለሶስተኛ ወገን ያከራዩ፣የተለያዩ አሰራሮችና ህጎችን የጣሱ በሚል 269 ባለሃብቶች የእርሻ ኢንቨሳትመንት ውላቸው እንዲቋርጥ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
የጥናት ቡዱኑ በወሰደው እርምጃ ቅሬታ ያሰሙት ባለሃብቶች በማህበራቸው አማካኝነት በትግራይ ተወላጅነታችን ምክንያት ጥቃት ደርሶብናል፥ አጥኚ ቡድኑ ኢሳትን በመሳሰሉ የሽብር ሚዲያዎች ሰለባ ሆኗል። የሚሉ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ተቃውሞአቸውን አሰምተው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል። እነዚህ ባለሃብቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመውን አጥኚ ቡድንና የልማት ባንኩን የበላይ ሃላፊዎች በልማት አደናቃፊነት በመፈረጅ አቤቱታቸውን ለፌደራልና የጋምቤላ ክልል አስተዳደር ማቅረባቸው ይታወሳል።
ባለሃብቶቹ ያወጡትን መግለጫና ያቀረቡትን አቤቱታ መነሻ በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ የሕወሃት አመራር በሆኑት አቶ አርከበ እቁባይ ልዩ ትእዛዝ ከፌደራልና ከጋምቤላ ክልል የተውጣጣ የቅሬታ አጣሪ ቡድን ላለፉት ሁለት ወራት የአቤቱታ አቅራቢዎችን ቅሬታ ሲመረምር ቆይቷል።ቅሬታቸውን በአካል ካቀረቡት 190 ባለሃብቶች ውስጥ 186 ያሕሉ ወደ ስራ እንዲመለሱ የውሳኔ ሃሳብ መተላለፉን ለማወቅ ተችሏል።
የቅሬታ አጣሪ ቡድኑ እስካሁን ወደ ስራ ያልገቡ በማለት 4 ባለሃብቶች የተረከቡት የእርሻ መሬት ሙሉ ለሙሉ ወደ መንግስት የመሬት ቋት ተመላሽ እንዲሆን በውሳኔው አስታውቋል። ወደ ስራ እንዲመልሱ ከተደረጉት 186 ባልሃብቶች ውስጥ 4 ያህሉ ብቻ የጋምቤላ ተወላጆች መሆናቸው ተገልጿል። በአሜሪካን የሚገኘው የኦክላንድ የምርምር ተቋም ባደረገው ጥናት በጋምቤላ ከተሰማሩት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።
በጋምቤላ የተሰማሩት የባለሃብቶች ማህበር አመራሮች ከስራቸው በታገዱ ጊዜ በሰጡት መግልጫ መንግስት ያቀረበውን የኢንቨስትመንት ጥሪ ተቀብለን ከገባነው ውስጥ በአጋጣሚ የትግራይ ተወላጆች እንበዛልን በማለት ምላሽ መሰጠታቸው ይታወቃል።