ሚያዚያ ፲፭(አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሙርሌ ጎሳ አባላት ተጠልፈው የተወሰዱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ አስረኛ ቀናቸውን ቢያስቀጥሩም እስካሁን ሰዎቹ ስላሉበት ሁኔታ በቂ መረጃ ሊገኝ አልቻለም።
ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓም የሙርሌ ጎሳ አባላት በኑዌር ኢትዮጵያውያን ላይ በሰነዘሩት ጥቃት፣ ከ143 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩት መቁሰላቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም ከ2 ሺ በላይ የቀንድ ከብቶች ደግሞ መዘረፋቸው መዘገቡ ይታወቃል። ድርጊቱን የፈጸሙት ሃይሎች የሚገኙበትን ቦታ ለማወቅ መቻሉንና ከበባም መደረጉን መንግስትን በመጥቀስ የአለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ጨምሮ ዜናውን ቢዘግቡም፣ እስካሁን ድረስ በኢህአዴግ መንግስት በኩል የተወሰደ እርምጃ የለም። መንግስት ዜጎቹን ለማስለቀቅ እያደረገ ስላለው ጥረት መግለጫ ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በበኩላቸው የተዛቡ መረጃዎችን እየሰጡ ነው።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ጥቃቱን የፈጸሙት ሰዎች በግዛቱ ውስጥ እንደሚገኙ እየታወቀ ለምን አፋጣኝ መልስ ሊሰጥ አልቻለም የሚል ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች መበራከታቸውን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር በሰጡት መግለጫ ጥቃቱን የፈጸሙት ሃይሎች በደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ሰዎችን የማስለቀቅ ስራ እንደሚሰራም አምባሳደሩ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን ግዛት ጠልቃ መግባቱዋን መንግስታቸው እንደማይደግፈው መገለጻቸው፣ የደቡብ ሱዳን መንግስትን አቋም በግልጽ ለማወቅ አላስቻለም።
የመከላከያ ሰራዊቱ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ዘልቆ ቢገባ በአካባቢው የሚታየውን አለመረጋጋት የበለጠ ያባብሰዋል በማለት ሶስት የደቡብ ሱዳን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ መንግስት የተጠለፉት ሰዎች በሽምግልና የሚመለሱበትን መንገድ ማፈላለግ ይኖርበታል ብለዋል። የሳልቫኪርና የቦማ ግዛት አስተዳዳሪ ሰዎቹ በአፋጣኝ እንዲመለሱና ለተጎዱት ቤተሰቦች ደግሞ ካሳ እንዲከፍሉ እነዚሁ ድርጅቶች ጠይቀዋል።
የደቡብ ሱዳን ፖለቲካ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተጽእኖ ማሰረፍ መጀመሩንም በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ። በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያሉ የደቡብ ሱዳን ኑዌሮች፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸሙት ጥቃት 21 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ያለአገባብ ተጠቃን ያሉ ኢትዮጵያውያን እስከ ትናንት ድረስ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን፣ 3 የኑዌር ተወላጆች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ዛሬ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንም አክለዋል።