መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ወሎ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የነበረው አቶ መኳንንት ካሳሁን እና የማእከላዊ ኮሚቴ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት አቶ ብስራት አቢ ከስራ እና ከመኖሪያ ቤታቸው ታግተው ከአንድ ወር በላይ አድራሻቸው መጥፋቱ ይታወሳል። ከሕግ አግባብ ውጪ ታፍነው የተወሰዱት ሰላማዊ ታጋዮቹን አድራሻ ለማግኘት ቤተሰቦቻቸው ባደረጉት ጥረት በማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ እና ከፍተኛ የሆነ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ መኳንንት ካሳሁን ያለበትን ሁኔታ ሲገልጽ ”ምሽት ላይ አምስት ሆነው እየመጡ ወንጀለኛ ነኝ ብለህ እመን በማለት በከፍተኛ ሁኔታ ይደበድቡኛል፡፡ ብስራት አቢም በከፍተኛ ሁኔታ ስቃይ ስለበዛበት ለመንቀሳቀስ ሁሉ ተቸግሯል፡፡” በእራሱ እና በትግል አጋሩ ላይ እየተፈጸመባቸው ስላለው ኢሰብዓዊ ድርጊትም ተናግሯል።
ካለምንም ወንጀል አድራሻው ጠፍቶ በከፍተኛ እንግልት በቤተሰቦቹ ጥረት ያለበት የታወቀው አቶ መኳንንት ካሳሁን የ28 ቀናት የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተሰጠበት ሲሆን በሁለቱም ላይ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል። የአያያዙን ሁኔታ አስመልክቶ ቤተሰቦቹ እንዳሉት ”ዴሞክራሲ አለ በሚባልበት አገር ላይ እንዴት ሰው ታፍኖ ይወሰዳል?” ሲሉ ስርዓቱን በዜጎች ላይ በዴሞክራሲ ስም እያደረሰ ያለውን ሰቆቃ ኮንነዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ ተስፋዬ እንዳሉት አቶ ብስራት አቢ ለስራ ጉዳይ በመጣበት ከደሴ ከተማ የታፈነ ሲሆን አቶ መኳንንት ካሳሁን ደግሞ ከስራ ቦታው ላይ ታፍኖ መወስዱን በተጨማሪም ድርጅታቸውም ሕልውና አደጋ ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለቱም ላይ በማእከላዊ ምርመራ ሰቆቃ እና ቶርቸር እንደተፈጸመባቸው ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት በምልክት ተናግረዋል። ሰላማዊ ታጋዮቹን ከደሴ ወደ ማእከላዊ አፍኖ መውሰድ ያስፈለገውም ሰብዓዊ መብታቸውን በመጣስ አካላዊ እና በማንነታቸው ላይ ያነጣጠሩ ጉዳቶችን ለማድረስ ሆን ታስቦ የተደረገ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ ሕዝቡን አግኝቶ ማነጋገር እንደማይቻልና በአፈና ውስጥ መሆናቸውን በእንደዚህ ዓይነት አፈና ውስጥ ሆነው ከገዥው ፓርቲ ጋር ድርድር ማድረግ ፓርቲያቸው ፈቃደኛ አለመሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
አቶ መኳንንት ካሳሁን ከየካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከስራ ቦታው ስፖርት ቤት ውስጥ ታርጋ በሌለው መኪና ተጭነው የመጡ ስድስት ታጣቂዎች አብረውት የነበሩትን በመሳሪያ አስፈራተው አስገዳጅ ሃይል በመጠቀም ታፍኖ መወሰዱን እና በመላው ቤተሰቡ በተለይ ወላጅ እናቱ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ መውደቃቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።