ከዘረኛና አምባገነን ስርዓት ለመላቀቅ ሁሉም ዜጎች ትግሉን እንዲቀላቀሉ በእስር የምትገኘው እየሩሳሌም ተስፋው ጥሪ አቀረበች

ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2008)

“ነጻ ለመውጣት የመጀመሪያው ራስን ከታሰሩበት የፍርሃት እስር ነጻ በመውጣት ትግሉን መቀላቀል ነው” ስትል የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አባልና በሽብር ወንጀል ክስ በእስር ላይ የምትገኘው እየሩሳሌም ተስፋው ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ገለጸች።

እየሩሳሌም ይህንን ደብዳቤ ግንቦት 7 1997ን ምክንያት በማድረግ ለህዝብ እንዲደርስ የፈለገችው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በእለቱ ለህዝብ አለመድረሱ በጽሁፉ ተገልጿል።

እየሩሳሌም በጽሁፏ በግንቦት 7 ፥ 1997 ዓ ም የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነቱ ያደረገውን ተሳትፎ እና እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ሰጥታለች።

“ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተማረረ ዜጋ አይገኝም ሁሉም ነጻነትን ይናፍቃል፥ ነጻ ለመውጣት ግን ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ይፈራል” ያለችው እየሩሳሌም፣ ገዢው ህወሃትን ለማስወገድና ህዝባዊ መንግስት ለመመስረት ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አትታለች።

ስትቀጥልም በተለይ ግንቦት 1977 ለብዙዎች ሞት፣ አካል መጉደልና፣ እስራት አብቅታለች ፥ መራራው ሳያልፍ ጣፋጭ፣ ሳይሞክሩ ትንሳዔ የለምና በባለፈው ከመጸጸት ያለፈው እልህ አሲዞን ይህንን ዘረኛና አምባገነን የሽፍታ ቡድን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መንግለን ለመጣል እንዘጋጅ ስትል ጥሪ አቅርባለች።

በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ መዝገብ አርበኞች ግንቦት 7ን ለመቀላቀል ሲሄዱ ተይዘዋል በሚል ክስ በእስር ላይ የምትገኘው እየሩሳሌም፣ አቶ በቅርቡ ባሰራጨችው ጽሁፍ አንዳርጋቸው ጽጌን አንስታለች።

የነጻነት ታጋዩ ጀግናው አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር አንድ ግቢ ውስጥ ብንኖርም፣ መገናኘት አልቻልንም በማለት “የአንተ መታፈን ትግሉን አያሽመደመደውም፣ ይበልጥ አጦዘው እንጂ። ለእኛ ከቤት መውጣት ምክንያት አንተ ነህ ፥ እኛ የአንተ ፍሬዎች ነን” ስትል አቶ አንዳርጋቸው የከፈለውን መስዋዕትነት ጠቅሳለች።