ከውጭ አገር ከሚገቡ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱ ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 27 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ ከውጭ ሃገር በሚገቡ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ተጠቃሚዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በበኩሉ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ምክንያት በማድረግ የሃገሪቱ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጣሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ባለፈው ወር ከነበረበት 8.1 በመቶ ወደ 8.2 በመቶ ማደጉን ሃሙስ አስታውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ከተለያዩ ሃገራት የሚገቡ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጣሸቀጦች በከፍተኛ መጠን በመቀነስ ላይ መሆናቸውን አስመጪ ነጋዴዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።

መድሃኒትን ጨምሮ አስቸኳይ ናቸው ተብለው የተፈረጁ እቃዎች ብቻ ቅድሚያ ዕድል ተሰጥቷቸው እየተስተናገዱ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል። በመንግስት የተወሰደው ይኸው መመሪያ በሌሎች መሰረታዊ የፍጆታ ቁሳቁሶች ላይ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉ ተመልክቷል።

ችግሩ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመዲናይቱ አዲስ አበባ ስኳርና ዱቄትን ለማግኘት በርካታ ሰዎች በሰልፍ እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የከተማዋ የንግድ ቢሮ በበኩሉ በመዲናይቱ የታየው የመሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦች እጥረት በአብዛኛው ከስርጭት ችግር ጋር የተያያዘ ነው ሲል ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ምላሽን ሰጥቷል። ተጠቃሚዎች እጥረቱ የቆየ በመሆኑ ከስርጭት ችግር የተባለው ምክንያት አሳማኝ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

ካለፈው አመት ጀምሮ በሃገሪቱ የተከሰተውን የስኳር እጥረት ለመቅረፍ መንግስት አለም አቀፍ ጨረታን በማውጣት ስኳር ለመግዛት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ይህንኑ ምርት ለማቅረብ አንድ የህንድ ኩባንያ የ71 ሚሊዮን ዶላር ጨረታን በማሸነፍ ከወራት በፊት ስኳር ማቅረብ ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ አቅርቦቱ ከፍላጎት ጋር ባለመጣጣሙ እጥረቱ ሊቀረፍ አለመቻሉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።

የንግድ ሚኒስትር በበኩሉ ከአለም አቀፍ ገበያ የተገዙ የስኳርና የዘይት ምርቶች ወደ ሃገሪቱ በመግባት ላይ መሆናቸውን ባለፈው ወር ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ እየቀነሰ መምጣት እና በሃገሪቱ ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖን በማሳደር የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲቀንስ ማድረጉን የፋይንናንስ ተቋማት ይገልጻሉ።

ይኸው የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት ሃገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው ሸቀጣሸቀጦች በመጠንና በአይነት እንዲቀንሱ ያደረጉ ሲሆን፣ ችግሩ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል ማድረጉን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስታውቀዋል።

ይሁንና መንግስት የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ባለመሆኑ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖን አያሳድርም ሲል ከተለያዩ አካላት የሚሰጡ ማሳሰቢያዎችን አስተባብሏል።