መጋቢት ፳፩ (ሃያ አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተለያዩ የውጭ አገር መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለኢትዮጵያውያን ለልማት እያሉ በብሄራዊ ባንክ በኩል ከሚያስተላልፉት ገንዘብ ውስጥ 50 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ ሳይውል ተቀምጦ እንደሚገኝ የብሄራዊ ባንክ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የውጭ አገር ዜጎች ለልማት እያሉ የሚያስገቡት ገንዘብ፣ በድርጅቶቹ ደካማ እቅድ አፈጻጸም ወይም በሌሎች ምክንያቶች ጥቅም ላይ ሳይውል ተከማችቶ እንደሚገኝ የሚገልጹት ምንጮች፣ የባንኩ ሃላፊዎችና የገንዘብ ሚኒስቴር ባላስልጣናት የአይ ኤም ኤፍ (IMF) ተቆጣጣሪ ኤክስፐርቶች ለቁጥጥር ሲመጡ የተለያዩ ሰበቦችን እየሰጡ እንደሚያታልሏቸው ተናግረዋል። ይህ ያለ ስራ ተከማችቶ የሚገኘው ገንዘብ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።