መስከረም ፳፩ (ኅያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-እንደ ነገረ ኢትዮጰያ ሪፖርተር ዘገባ ከአምስቱ እስረኞች መካከል አንዱ የሆነው የአንድነት ፓርቲው አቶ ዳንኤል ሽበሽ ጨለማ ቤት ታስሮ ይገኛል።
የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሀምሌ 14/2007 ዓ.ም ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲለቀቁ ወስኖላቸው የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሽበሽና አቶ አብርሃም ሰለሞን ለመጪው ጥቅምት 3 ቀን የተቀጠሩት ፤ ተጠይቆባቸው የነበረው ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው።
አምስቱ ተከሳሾች፤ የተጠየቀባቸው ይግባኝ “ተቀባይነት ይኖረዋል ? ወይስ አይኖረውም?” የሚለውን ጉዳይ ለመወሰን ዛሬ መስከረም 21/2008 ዓ.ም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቀጥረው ነበር።
በቀጠሮው መሰረት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብርሃም ሰለሞን ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኙት አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ ዳንኤል ሽበሽ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ ዳንኤል ሽበሽ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በውስጥ ይግባኙ ተቀባይነት አግኝቶ ቀጠሮ እንደተሰጠባቸው ከመዝገብ ቤት ለማወቅ ተችሏል።
በቃሊቲ የሚገኙት ሶስቱ እስረኞች መቀጠራቸው ከታወቀ በኋላ ከቂሊንጦ እስር ቤት ዘግይተው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሱት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብርሃም ሰለሞንም በቢሮ ተመሳሳይ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
እነ ሀብታሙ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት አቃቤ ህግ ያልተገኘ ሲሆን፤ ስለ ቀጠሮው ምንም አይነት ምክንያት እንዳልተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ከተከሳሾቹ መካከል በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኘው አቶ ዳንኤል ሽበሽ በጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና ከቤተሰቦቹም ጋር መገናኘት እንደማይችል ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር ተናግረዋል፡፡