ከእስር ቤት በግድ ተጎትተው መውጣታቸውን ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ገለጹ
(ኢሳት ዜና የካቲት 8 ቀን 2010ዓ/ም) በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከሰው ላለፉት 9 ዓመታት በእስር ያሳለፉት ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ በመፈታታቸው ብዙም የተሰማቸው የተለዬ ደስታ እንደሌለ ገልጸዋል። ልጆቻቸው አንደኛው በትግል ላይ ሌላኛዋ ደግሞ በስደት ላይ በመሆናቸው በአካል እንዳላገኙዋቸውም ተናግረዋል።
“ብዙ ስቃይ ያዩት አባሪዎቼ በእስር ቤት ሆነው የእኔ መፈታት ምንም ደስታ አልሰጠኝም” ያሉት ወ/ሮ እማዋይሽ፣ “ ማረሚያ ቤታችን ነጻ ብሎሻል። ሌሎችም ቀጥለው ይወጣሉ፣ አንች አሁን ውጭ፣ የሚቀር ሰው የለም” ተብሎ ተነግሯቸውና ተጎትተው እንደወጡ ተናግረዋል። በእስር ቤት አሰቃቂ ህይወት መግፋት የተለመደ ቢሆንም ዋናው ጽናት ነው ያሉት ወ/ሮ እማዋይሽ ፣ በተለይ አቶ አንዳርጋቸው ያሉበት ሁኔታ እጅግ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው አርበኞች ግንቦት7ትን ለመቀላቀል ሲል ተይዞ ላለፉት 4 ዓመታት በእስር ቤት ያሳለፈውና ትናንት የተፈታው ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ በእስር ቤት ውስጥ ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን መመልከቱን ተናግሯል። በእስር ቤት ውስጥ የእጅና እግር ጥፍሮቻቸው ተነቃቅለው ለስቃይ የተዳረጉ ሰዎች መኖራቸውንም ወጣት ብርሃኑ ተናግሯል።
“የመጨረሻው መጀመሪያ ላይ ነን። ጫፉን ይዘነዋል እንጅ አልጨረስነውም። ትግሉ መቀጠል አለበት። እያንዳንዱ ሰው በከፈለው መስዋዕትነት፣ በእያንዳንዱ ጠብታ እዚህ ተደርሷል። ከእንግዲህ በአገራችን በነጻነት እንድንኖር ከመተቻቸትና ከመናናቅ ወጥተን ምንድነው የሚያስፈልገን በሚለው ላይ መነጋገር መጀመር አለብን። ህዝቡ በጋራ ቆሞ ትግሉን መቀጠል አለበት። እኛም የህይወት መስዋዕትነት መክፈል ካለብን እንከፍላለን።” ሲል አክሏል።