ኢሳት (መስከረም 23: 2009)
በቢሾፍቱ ከተማ ዕሁድ ከእሬቻ በዓል አከባበር ጋር በተገናኘ የተገደሉ ሰዎችን ድርጊት በማውገዝ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።
በሃዘን ድባብ ውስጥ በምትገኘው የደብረዘይት ከተማ እንዲሁም ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተሞችና በምስራቅ አርሲ ዞን ከእሁድ ጀምሮ ህዝቡ ተቃውሞን እያሰማን እንደሚገኝ ነዋሪዎችን ለኢሳት አስታውቀዋል።
በምስራቅ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ የገጠር ከተሞች እንዲሁም በሻሸመኔና አጎራባች ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞው በመካሄድ ላይ ሲሆን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የሃይል ዕርምጃን እየወሰዱ እንደሆነ ታውቋል።
ይሁንና በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ የደረሰውን ጉዳት በአግባቡ ለማወቅ እንዳላስቻለ ከኢሳት ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ እማኞች የገለጹ ሲሆን የመንግስት ተሽከርካሪዎችና ጽ/ቤቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው በመሰራጨት ላይ ያሉ መረጃዎች አመልክተዋል።
ዕሁድ አሰቃቂ ነው የተባለው ድርጊት በደረሰባት የደብረዘይት ከተማም ምሽቱን ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተኩስ ድምፅ ሲሰማ ማደሩንና ድርጊቱ ሰኞ ረፋድ ድረስ መቀጠሉን ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ነዋሪነታቸው በአምቦ ጉደር የሆነ ነዋሪዎች በከተማዋ የመንግስት ስራን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራ ማቆማቸውንና ነዋሪዎች ሃዘኑን በተለያዩ መልክ እየገለጸ እንደሆነ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ነዋሪነታቸው በዝዋይ ባቱ የሆነ ዕማኞች ደግሞ በሌሎች የኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በዝዋይ ከተማና ዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ መሆኑን ለዜና ክፍላችን አስታውቀዋል።
ዕሁድ ምሽት በአካባቢው ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር በተገኛኘ በትንሹ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራ ማቆማቸውን ተናግረርዋል።
የህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የዝዋይ አዳሚቱሉ መንገድ ዝግ መሆኑን ከነዋሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።
በምስራቅ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ሲባል የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎች የሃይል ዕርምጃን በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ከኢሳት ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች አክለው አስታውቀዋል።
ይሁንና በየከተሞቹ ያለው ተቃውሞ ዕልባት ባለማግኘቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ማወቅ እንዳልተቻለ እማኞች አክለው ገልጸዋል።