ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በኩል ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት ለመሰደድ የሚሞክሩ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰበው የሃረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ባለፉት ስድስት ወራቶች ብቻ ሃረር ከተማን አቋርጠው በሶማሌ ክልል በኩል ድንበር ለማቋረጥ ሙከራ ያደረጉ ከ1ሺ 700 በላይ ወጣቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉን ፖሊስ ለሃገር ውስጥ መገኛኛ ብዙሃን ገልጿል።
ባለፈው አመት በተመሳሳይ ሁኔታ 3ሺ ወጣቶች ከሃገር ለመሰደድ በሞከሩ ጊዜ በጸጥታ ሃይሎች የተያዙ ሲሆን፣ ድርጊቱ መባባስን አሳይቶ በስድስት ወራቶች ብቻ ወደ ሁለት ሺ የሚጠጉ ወጣቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
የክልሉ ፖሊስ የወጣቶቹን ስደት ለመግታት የተለያዩ የቁጥጥር ስራዎችን ተግባራዊ ቢያደርግም ድንበር በማቋረጥ ከሃገሪቱ የሚሰደዱ ወጣቶች ቁጥር መቀነስን ከማሳየት ይልቅ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑ ተመልክቷል።
በሃረር ከተማ በኩል ከኢትዮጵያ በመሰደድ ላይ ካሉ ወጣቶች በተጨማሪ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ መልኩ በኬንያና ሱዳን በኩል ከሃገሪቱ በመሰደድ ላይ መሆናቸውን የስደተኛ ተቋማት ይገልጻሉ።
ባለፈው አመት ብቻ ወደ 90ሺ አካባቢ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ጦርነት ዕልባት ወደ አላገኘባት የመን የተሰደዱ ሲሆን፣ ችግሩ አሁም ድረስ መቀጠሉን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ የመለክታል።
በሃረር ከተማ እየተባባሰ የመጣውን ይህንኑ የወጣቶች ስደት ለመቆጣጠር የሃረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመተባበር ጥረትን እያደረገ እንደሆነ የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።
ወጣቶቹን በማዘዋወሩ ድርጊት ተሰማርተዋል የተባሉ 15 ሰዎች ከ 1 እስከ 10 አመት በሚደርስ የእስራት ቅጣት የተላለፈባቸው ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር ከዋሉት በተጨማሪ ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ ወጣቶች ድንበር ማቋረጣቸው ይነገራል።