(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2010) በእንግሊዝ ሃይሎች ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶች በአደራ መልክ ሊመለሱ መሆኑ ተነገረ።
አንድ ክፍለ ዘመን ሙሉ በእንግሊዝ ተዘርፈው የቆዩት የኢትዮጵያ ቅርሶች በእዳ መልክ ለተወሰነ ጊዜ ተመላሽ እንደሚደረጉ ታውቋል።
በእንግሊዝ ሙዚየም የሚገኙ እነዚሁ ቅርሶች በአጼ ቴድሮስ ጊዜ ከመቅደላ የተዘረፉ መሆናቸውም ተነግሯል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1868 እንግሊዞች በአጼ ቴድሮስ የታሰሩ ዜጎቻቸውን ለማስለቀቅ ወደ ኢትዮጵያ ሲዘምቱ የተመዘበሩ ቅርሶች በርካታ ናቸው።
አጼ ቴድሮስ በመቅደላ እጃቸውን ላለመስጠት እራሳቸውን በገዛ ሽጉጣቸው ሲያጠፉ መቅደላ ላይ እንግሊዞች ያገኙት የንጉሱን ልዩ ልዩ ቁሶች ነበር።
በዚያን ጊዜ በወቅቱ ታዳጊ የነበረውን የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ቴድሮስን ጨምሮ የንጉሱን ቁሶች ወደ እንግሊዝ ወስደዋል።
አለማየሁ ቴድሮስ በአንድ እንግሊዛዊ ወታደር እንክብካቤ ሲደረግለት ቢቆይም በደረሰበት የስነ ልቦና ችግርና ሕመም በዛው በእንግሊዝ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል።
መቃብሩም በእንግሊዝ ንጉሳውያን ቤተሰቦች የመቃብር ስፍራ ይገኛል።
በዚያን ወቅት የተዘረፉት የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲመለሱ እንግሊዝ በተደጋጋሚ ብትጠየቅም አሻፈረኝ ብላ መቆየቷም የሚታወስ ነው።
በተለይም ግሊመር ኦፍ ሆፕ የተባለ ድርጅት ቅርሶቹን ለማስመለስ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካለት ቆይቷል።
አሁን ከእንግሊዝ የተሰማው ዜና ግን ቅርሶቹን በውሰት ለኢትዮጵያ ለመመለስ መስማማቷ ነው የተነገረው።
በእንግሊዝ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች በአደራ መልክ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ አንድ ለውጥ ነው ተብሏል።
ወደፊት ደግሞ በዘላቂነት ቅርሶች የሚመለሱበት ሁኔታ ይመቻች ይሆናል የሚል ተስፋም አሳድሯል።ይሕን ሁኔታ ግን የቅርስ ተቆርቋሪው አቶ ኪዳኔ አለማየሁ እና አለምአቀፍ የህግ ባለሙያው ዶክተር ያዕቆብ አለማየሁ እንግሊዝ በውሰት ወይንም በእዳ የተወሰኑ ቅርሶችን እመልሳልሁ ማለቷ በሁዋላ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ለማንሳት እንዲያመቻት ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ቅርሶቹ ከእንግሊዝ ሙዚየም ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ በውሰት መልክ ሲመጡ በአግባቡ እንደሚያዙና ለሃገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ጎብኝዎች ክፍት እንደሚደረጉ ኳርትዝ አፍሪካ የተባለው ድረ ገጽ ዘግቧል።
በእንግሊዝ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቅርሶች የተቀመጡት ቪክቶሪያ እና አልበርት በተባሉ ሙዚየሞች ነው።
ቅርሶቹ በ15 ዝሆኖች እና በ 200 በቅሎዎች ተጭነው መወሰዳቸውንም ሪፖርቶች ያመለክታሉ።