ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ  የተሰጠ መግለጫ

ኢሳት (ግንቦት ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) በሃገር ቤትና በአካባቢው ሲያስተላልፍ የነበረው የሳተላይት ስርጭት እንደተለመደው በአገዛዙ ጭንቀትና ስጋት ምክንያት በህወሃት ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ስርጭቱ እንዲቋረጥ አድርጎ ህዝቡ መረጃ እንዳያገኝ ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ ይገኛል።

በኢሳት ምክንያት እንቅልፍ ያጣው የህወሃት /ኢህአዴግ አገዛዝ አሁን ደግሞ እንደተለመደው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሳተላይት ስርጭቱ እክል እንዲገጥመው አድርጓል። ይሁን እንጂ የኢሳት አመራር አባላትና የቴክኒክ ቡድን አባላት ስርጭቱን በአጭር ጊዜ ለመመለስና አማራጮችን ለመጠቀም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢሳት ማኔጅመንት የሳተላይት ስርጭቱ በቅርቡ እንዲመለስ የተለያዩ አማራጮችን በማየት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ለተከበራችሁ አድማጮችና እና ተመልካቾች ማሳወቅ ይወዳል። በቅርቡም በአዲስ ሳታላይት  በተለያዩ ፍሪኮንሲዎች የምንመልስ መሆኑን  እናስታውቃለን።

የሳተላይት ስርጭቱ በአገዛዙ ተፅዕኖ ምክንያት ለጊዜው እክል ቢገጥመውም፣ በናይል ሳት ሲተላለፍ የቆየው የሬዲዮ ስርጭት አሁንም እየተላለፈ በመሆኑ በቅርቡ እስክንመለስ ድረስ ይህንኑ አማራጭ መጠቀም የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።

አገዛዙ ምንም አይነት የአዋጅ ጋጋታ ቢደረድርም ህዝቡ ከፍርሃት ወጥቶ ኢሳትን መከታተል በመቀጠሉም ሌላ ሙከራ በማድረግ ኢሳትን በሰበብ አስባቡ በመወንጀል ይፋዊ ክስ እስክመመስረት መድረሱም ይታወቃል።

ስለሆነም ኢሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያና አካባቢው ተመልካቾች የሳተላይት ስርጭቱን እንደገና እስኪጀምር ድረስ በናይል ሳት ሬዲዮ ፥ እንዲሁም  በኢንተርኔት አገልግሎት በዩቱዩብና በፌስቡክ ማህበራዊ መገናኛዎች ስርጭታችንን ልትከታተሉ እንደምትችሉ በአክብሮት እናስታውቃለን።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) ማኔጅመንት