ኢሳት (ሚያዚያ 4 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ የቡና ውጭ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ መንግስት ቡና ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጭ ለአለም አቀፍ ገበያ እንዳይቀርብ ጥሎት የነበረን እገዳ አነሳ።
የምርት ገበያ ከስምንት አመት በፊት መቋቋሙን ምክንያት በማድረግ ሁሉም ቡና ላኪ ድርጅቶች ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡትን ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲያደርጉ ተደርጎ መቆየቱ ይታወሳል። ይሁንና ለስምንት አመት ሲሰራበት የቆየውን ይህንኑ መመሪያ መንግስት ከተያዘው ወር አጋማሽ ጀምሮ ለማንሳት መወሰኑን መቀመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው ትራቦካ የተሰኘ የቡና ንግድ ኩባንያ አስታውቋል።
የኩባንያው መስራችና ሃላፊ የሆኑት ሜኖ ሲሞን በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰባት የኩባንያው አባላት መንግስት ቡና ከምርት ገበያው ውጭ ለአለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርብ መወሰኑን እንዳረጋገጠላቸው ለዴይሊ ኮፊ ኒውስ መጽሄት ገልጿል።
ቡናን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች በቅርቡ ምርታቸውን በቀጥታ ለአለም አቀፍ ቡና ገዢዎች ማቅረብ እንደሚጀምሩ የኔዘርላንድ ቡና ኩባንያ አስታውቋል። መንግስት ለአለም አቀፍ ገበያ የሚቀርብን ቡና በጥራትና በዋጋ የተሻለ ለማድረግ በሚል በሃገሪቱ ያሉ ሁሉም ቡና ላኪ ድርጅቶች ምርታቸውን በምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲሸጡ መመሪያ ተግባራዊ አድርጎ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
መንግስት ለስምንት አመት ጥሎ የቆየውን እገዳ ለማንሳት መወሰኑ ነጋዴውንና ገዢዎችን በቀጥታ ለማገናኘት ትስስርን ለማጠናከር እንደሚረዳ የትራቦካ ሃላፊው ለመጽሄቱ አስረድተዋል።
ካለፉት ሶስትና አራት አመታት ወዲህ የኢትዮጵያ የውጭ ቡና ንግድ ገቢ ከተጠበቀው በላይ በማሽቆልቆል የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲቀንስ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን የመንግስት ባለስልጣናት ይገልጻሉ።
በርካታ ግለሰቦች ህገወጥ የቡና ንግድ ፈቃድን በማውጣት ቡናን በህገ-ወጥ መንገድ ለገበያ አቅርበዋል ተብለው ባለፈው ወር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
ሃገሪቱ በተደጋጋሚ ያጋጠማት የውጭ ቡና ንግድ ማሽቆልቆልን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እንዲቋቋም የተደረገ አንድ ቡድን ችግሩን እንዲያጠና ተደርጎ ቆይቷል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ጥናቱን መሰረት አድርጎ ይሁን በሌላ ምክንያት የታወቀ ነገር የለም።
ለስምንት አመት የቆየው እገዳ መነሳት ኢትዮጵያ በአለም የምትታወቅባቸውን የቡና አይነቶች በሚፍለገው መጠን ዳግም እንድታቀርብ የሚያደርግ እንደሆነም የኔዘርላንዱ ኩባንያ አክሎ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ብቻ ቡናን ለአለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርቡ ተገደው የነበሩ ነጋዴዎች መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ቡናን ባገኛችሁት ዋጋ ሽጡ እያለ ሲያስገድዳቸው መቆየቱን ሲገልፁ ቆይተዋል።
ይህንኑ ድርጊት የተቃወሙ ነጋዴዎች ቡናን ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ቢጀምሩም መንግስት አዲስ መመሪያን ለማውጣት ለውጭ ገበያ መቅረብ ያለበትን ቡና ለሃገር ውስጥ ገበያ በሚያቀርቡ ነጋዴዎች ላይ እስከ አምስት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚጣል መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።
ይሁንና በተገኘው ዋጋ ቡናን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ የተገደዱ ነጋዴዎች ዕርምጃው ኪሳራን የሚያስከትል ነው በማለት ከንግዱ ራሳቸውን ሲያገሉ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
የእገዳው መነሳት የቡና ነጋዴዎች የነጻ ገበያ መርህን እንዲከተሉ የሚያደርግ እንደሆነም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።