ጥር 18 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ለ አንዲት ኢትዮጵያ ለመታገል የወሰነው የ ኦሮሞ ነፃነት ግንባርና የግንቦት 7 ለፍትህ፣ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ በመጪው ፌብሩዋሪ ወር በሚኒሶታ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ዘ-ሀበሻ ዘገበ።
በኦነግ የሰሜን አሜሪካ አስተባባሪና የህግ አማካሪ የሆኑትን ዶክተር ነሩ ደደፎን በመጥቀስ ዘ-ሀበሻ እንደዘ ገበው በመቺው ወር አጋማሽ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የሚካሄደው ታላቅ ስብሰባ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያካተተ እና በቀጣዮቹ የትግል አቅጣጫዎች ዙሪያ ግልጽ አቋም የሚንጸባረቅበት ነው።
“ስብሰባው፤ ኦነግ ለ አንዲት ኢትዮጵያ በጋራ ለመታገል ከወሰነ በሁዋላ የሚደረግ የመጀመሪያው ታላቅ ስብሰባ ይሆናል”ያሉት ዶክተር ኑሩ ደደፎ፤ የሁለቱ ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች በአካል በመገኘት ስለ ዓላማቸውና ስለትግላቸው አቅጣጫ ለተሰብሳቢው እንደሚያስረዱ ገልጸዋል።
ስብሰባው የሚካሄድበት ትክክለኛ ቀንና ሰአት ሰሞኑን ይፋ እንደሚሆን ዶክተር ኑሩ ቢናገሩም፤የዘ-ሀበሻ ምንጮች ፌብሩዋሪ 10 እን ደሆነ ጠቁመዋል።
በ ኦነግ በኩል እርሳቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች ፤በግንቦት 7 በኩል ደግሞ ዶክተር ብርሀኑ ነጋና ሌሎች አመራሮች በሚሳተፉበት በዚህ ስብሰባ፤ ሁለቱ ድርጅቶች ለአንዲት ኢትዮጵያ አንድነት ለመታገል የደረሱበት ስምምነት ይበሰራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጋዜጣው አመልክቷል።