ከአዲስ አበባ 430 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ አናለማ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር የሚገኙ ጡረተኞች በማኀበር ተደራጅተው ሲሰሩበት ከነበረው መሬት በድንገት መፈናቀላቸውን ገለጹ

ግንቦት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጡረተኞቹ የጎባና የአካባቢው ጡረተኞች ማኀበር በሚል ተደራጅተው በ1991 ዓ.ም፣ 200 ሄክታር መሬት ተረክበው
ሲሰሩ እንደነበር በመሃል 75 ነጥብ 25 ሄክታር መሬት መነጠቃቸውን በአሁን ወቅት ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ
አውጥተው እያለሙ ያሉትን መሬት ሙሉ በሙሉ መነጠቃቸውን ገልጸዋል፡፡ መሬቱ ለ25 ዓመታት ተዋውለን የተረከብነው
ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በ30 ሄክታር መሬት ላይ ከ75 ሺ ብር በላይ ለትራክተር ኪራይ፣ ለዘር መግዣ
አውጥተን ልንዘራ በተዘጋጀንበት ወቅት የጎባ ዞን ኢንቨስትመንት ቢሮ ግልጽ ቦታውን አላለማችሁትም በሚል ምክንያት
መሬቱን እንድናስረክብ አስገድዶናል፤ እኛ ግን መሬቱን ጦም አሳድረነው አናውቅም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ማኀበሩ በጎባና አካባቢዋ የሚኖሩ 264 ጡረተኛ አባላት ያሉት ሲሆን እነዚህ አባላትም ከ1ሺ500 በላይ ሰዎችን
በስራቸው እንደሚያስተዳድሩና በአሁኑ ሰዓት አባሎቻችን ከነቤተሰባቸው በችግር ላይ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡