ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተነሳት ተቃውሞ አሁንም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደቀጠለ ነው

ኢሳት (ጥር 10 ፥ 2008)

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በተቃውሞ ለሚሳተፉ አካላት ጥረትን ቢያቀርብም ዳግም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች መቀጠሉ ተገለጠ።

በምስራቅ ሃረርጌ መኢሶ አካባቢ በሳምንቱ መገባደጃ የተጀመረው ተቃውሞ ለአራተኛ ቀን መቀጠሉንና ነዋሪዎች በጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱ ግድያዎች እንዲያቆሙ መጠየቃቸው ታውቋል።

ሰኞ የክልሉ መንግስት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተቃውሞ የተሳተፉ አካላትን በሆደ-ሰፊነት እንደሚመለከት በመግለፅ ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይሁንና ሁለተኛ ወሩን የዘለለው እና አለም-አቀፍ ትኩረትን ስቦ የሚገኘው ይኸው ተቃውሞ ማክሰኞም ከምስራቅ ሃረርጌ አካባቢዎች በተጨማሪ በምስራቅ ወለጋ ሲካሄድ መዋሉን ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

በምዕራብ ሃረርጌ ቀጥሎ የሚገኘውን ተቃውሞ ተከትሎም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ሃይል በስፍራው ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም ከዚህ በፊት ከተገለጸው ከስድስት ከፍ ማለቱ ታውቋል።

በአካባቢው ያለው አለመረጋጋትም የሟቾችን ቁጥርና ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን በአግባቡ ለማወቅ አስቸጋሪ ማድረጉን ነዋሪዎች መግለጻቸው ታውቋል።

በምስራቅ ወለጋ አካባቢም ተመሳሳይ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ እንደሚገኝ የገለፁት ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ማክሰኞ የከተራ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በተከበረበት ወቅት ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ሃይል ከተለመደው ውጭ ተሰማርቶ መገኘቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች በበኩላቸው ረቡዕ በመላው ሃገሪቱ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ በርካታ የሰው ሃይል እንዲሰማራ መደረጉን አስታውቀዋል።

የበዓሉ ዝግጅቶች በሚካሄድባቸው ስፍራዎችም ከፀጥታ ሃይሎች በተጨማሪ ተባብረው የሚሰሩ ወጣቶች መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማክሰኞ ምሽት ገልጸዋል።