ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የሚኒስትር መ/ቤቶች የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች በደሞዝ ልዩነት ቅሬታ አሰሙ

ህዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “ሁላችንም የህዝብ ግንኙነት ሠራተኞች ብንሆንም ጥቂት ሠራተኞች በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፅ/ቤት ስልጠና ስለተሰጣቸው ብቻ ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ይደረግላቸዋል” በማለት ጋዜጣው ዘግቧል።

በኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ለ13 ቀናት የሚሰጠውን ስልጠና የተከታተለ ባለሙያ ደሞዙ ከ2250 ብር ወደ
4150 ብር ከፍ እንደሚል የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በአንድ ሙያ ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች የዚህን ያህል የደሞዝ ልዩነት መፈጠሩ ከፍተኛ የሞራል ጉዳት አድርሶብናል ብለዋል፡፡ እኒሁ አቤቱታ አቅራቢዎች ፊርማ አሰባስበው ለመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ማስገባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው የሚሰጠው ለተወሰኑ ሠራተኞች ብቻ መሆኑን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ይሄም ለተፈጠረው ልዩነት ሌላው ችግር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ሁሉም ፖሊሲውን ለማስፈፀም ብቁ ናቸው ተብለው መቀጠራቸውን በመግለፅም በአንድ መ/ቤት በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ ላይ እየሠሩ የዚህን ያህል የደሞዝ ልዩነትን መኖሩ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ይናገራሉ እንደጋዜጣው ዘገባ

ከዚህ ቀደም በሚሠሩበት መ/ቤት ችግሩን ለሃላፊዎቻቸው ቢያቀርቡም በሚቀጥለው ወር ጠብቁ እየተባሉ አንድ አመት እንዳለፋቸው የሚናገሩት ሠራተኞቹ፤ በመጨረሻም ችግራቸውን ለመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ለማቅረብ መገደዳቸውን ገልፀዋል፡፡

ስልጠናውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን እና የፅ/ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በየሁለት ወሩ ለ13 ቀናት እንደሚሰጡ በዘገባው ተጠቅሷል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው፤ የንግግር እና የመፃፍ ችሎታቸውን የበለጠ ለማዳበር እና የመ/ቤታቸውን አላማዎች ማብራራት እንዲችሉ የፖሊሲ ስልጠና እንደሚሰጥ ለጋዜጣው ገልጸዋል።

የህዝብ ግንኙነት ስራ በራሱ የፖለቲካ ተሿሚም ስለሆነ የተለያዩ ወቅታዊ ስልጠናዎች ለባለሙያዎቹ እንደሚሰጣቸው የተናገሩት አቶ ሽመልስ፤ ሠራተኞቹ ያሉባቸውን ችግሮች ለሀላፊዎቻቸው አቅርበው መፍትሔ ካላገኙ ወደ እኛ መምጣት ይችላሉ ብለዋል፡፡