ሚያዚያ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ብሉምበርግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በረሃብ የተጠቁት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ቀድሞ ከተገለጠው 10 ሚሊዮን በእጥፍ ጨምሮ 20 ሚሊዮን ደርሶአል፡፡ ይህ አሃዝ በምግብ ለስራ የታቀፉትና የምግብ እርዳታ የሚሰፈርላቸውን 8 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሁም፣ በከተሞች በምግብ እጥረት የተጠቁትን 10 ሚሊዮን ዜጎች አይጨምርም፡፡
በድርቅ ከተጎዱ 443 ወረዳዎች መካከል 219 ወረዳዎች ከፍተኛ የሆነ የምግብ ችግር አጋጥሞአቸዋል፡፡ ከፍተኛ የምግብ ችግር በእንግሊዝኛ very severe lack of food security ማለት ከፍተኛ የሆነ ሞት የሚያስከትል፣ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጣጠነ ምግብ እጥረት የሚፈጥር እንዲሁም ሊመለስ የማይችል የንብረት መውደም የሚያሰከትል መሆኑን ጋዜጣው መንግስትን በምንጭነት በመጥቀስ ዘግቦአል፡፡
ኢትዮጵያ 800 ወረዳዎች ያሉዋት ሲሆን፣ 443 ቱ ወረዳዎች ወይም 55 በመቶ የሚሆነው አካባቢ በድርቅ ተጠቅቶአል፡፡ ድርቁን ለመቁዋቁዋም 1 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ መንግስትና የውጭ አገር መንግስታት ወደ ግማሥ የሚጠጋውን ገንዘብ አቅርበዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ደግሞ 122 ሚሊዮን ዩሮ ለግሶአል፡፡
ከውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚ/ር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ድርቁ በተከሰተባቸው በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በድሬዳዋ፣ በሶማሌ በሚገኙ 189 ወረዳዎች 5 ነጥብ 8 ሚሊየን ህዝብ ለመጠጥ ውሀ እጥረት ተጋልጦአል።
በዚህም አስቸኩዋይ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ማከናወን ካልተቻለ የከፋ ችግር ሊገጥም ይችላል።ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግስት 750 ሚሊየን ብር፣ ዩኒሴፍና ሌሎች ለጋሾች 450 ሚሊየን ብር፣ ክልሎች 320 ሚሊየን ብር በድምሩ 1 ነጥብ 52 ቢሊየን ብር ወጪ በማድረግ የነበሩ የውሀ ጉድጉዋዶችን የማደስ፣ የከርሰ ምድር ውሀ ቁፋሮ ማካሄድ፣ በቦቴ የውሀ እደላ የማከናወን ስራዎች እየተካሄደ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር እስካሁን የተከናወነው አመርቂ አይደለም ይላል።
በተለይ የውሀ አማራጭ የሌለባቸው አካባቢዎች በቦቴ ውሀ የማደሉ ስራ ካለው አቅም ጋር የማይመጣጠን መሆኑ በከፍተኛ ችግርነት ተጠቅሶአል።