(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2010) አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ በነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ምክንያት ከትግራይ ክልል ውጪ በርካታ ከተሞች በጨለማ ተውጠው እንደነበር ተገለጸ።
በግልገል ጊቤ ግድብ የሃይል ማመንጫ ጣቢያ በተፈጠረ ችግር የኢትዮጵያ ከተሞች በጨለማ መዋጣቸው ብዙዎችን ግራ አጋብቶ እንደነበር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ችግሩ ተፈቶ መብራት መለቀቁን ቢገልጽም የተወሰኑ ከተሞች ግን አሁንም በጨለማ እንደተዋጡ መሆናቸው ታውቋል።
በግልገል ጊቤ የሃይል ማመንጫ የተፈጠረው ችግር የኤሌክትሪክ መቋረጥ በማስከተሉ የኢትዮጵያ በርካታ ከተሞች በጭለማ ተውጠው ነበር።
በመዲናዋ ሙሉ ለሙሉ የኤሌክትሪክ ሃይል በመቋረጡ የአለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በጭለማ ውስጥ ነው ያደረችው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የሃይል ማቋረጥ ችግሩን ለመፍታት ሌሎች ማመንጫዎችን ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጿል።
ከነዚሁም መካከል የጣና በለስና የፊንጫአ መስመሮች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ሃይል ሙሉ በሙሉ ተመልሷል ነው ያሉት።የተወሰኑት ከተሞች ግን አሁንም በጨለማ እንደተዋጡ መሆኑ ተሰምቷል።
ትላንት በመላ ሃገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ሲቋረጥ በትግራይ ክልል ግን አለመቋረጡ ተገልጿል።
የትግራይ ክልል የሃይል ምንጭ ከተከዜና ጣና በለስ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ከተዘረጉ መስመሮች የሚገኝ ነው ።
በኢትዮጵያ በግልገል ግቤ የሃይል ማመንጫ ግድብ ምክንያት ወደ ኬንያ የሚሄደው ውሃ በመቀነሱ የቱርካና ሃይቅ መጠኑ እያሽቆለቆለ መሆኑ ይነገራል።
በዚሁም ምክንያት ኬንያ በኢትዮጵያ ላይ ተቃውሞ ስታቀርብ ቆይታለች።
በሃገሪቱ ያለው አገዛዝ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሃይል እጥረት ባለበት ሁኔታ ለውጭ ጎረቤት ሃገራት ኤሌክትሪክ ለመሸጥ ስምምነት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።