ከታንዛኒያ ወደ ማላዊ ሲጓዙ የነበሩ 42 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞተው ተገኙ

ሰኔ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የታንዛኒያ ያገር ውስጥ ምክትል ሚኒስትርን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፤ በከባድ መኪና  እንደ ዕቃ  ከሁዋላ ታሽገው ወደ ማላዊ ሲጓዙ ከነበሩት 120 ሰዎች መካከል 42 ቱ ሞተዋል።

ሚኒስትሩ ፔሬሪያ ሲሊማ እንዳሉት ስደተኞቹ የመጡት ከኢትዮጵያ ሲሆን፤የሞቱትም  ከትራኩ  የሁዋላ ክፍል ተጨናንቀው በመታሸጋቸው ሳቢያ አየር አጥሯቸው ነው።

ታንዛኒያ እና ማላዊ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራቸው  የሚፈጠርን ግጭት እና ድርቅን በመሸሽ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ ለሚፈልጉ ኢት ዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን ስደተኞች ፤እንደመሸጋገሪያ እየሆኑ መምጣታቸውን ቢቢሲ አመልክቷል።

በተመሣሳይ የዛሬ ሳምንት ከማላዊ ወደ ደቡብ አፍሪካ በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ 47 ኢት ዮጵያውያን ስደተኞች  ማላዊ ሀይቅ ውስጥ ሰጥመው ማለቃቸው ይታወሳል።

የ አገር ውስ ጥ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ኔት ወርክ አፍሪካ ፕሮግራም  እንዳብራሩት፤ 127 ስደተኞች በሁለት  መኪኖች  ተሳፍረው ከኢትዮጵያ ጉዞ ይጀምራሉ።

ከዚያም የኬኒያን መዲና ናይሮቢን በማቆራረጥ ወደ ታንዛኒያ-አሩሻ ከተማ   እንደደረሱ፤ ወደ ማላዊ ወደሚሄድ ሌላ  ከባድ መኪና ይዘዋወራሉ።በትራኩ የሁዋለኛ ክፍል እንደ ዕቃ ታሽገው የማላዊ ጉዟቸውን ይጀምራሉ።

ስደተኞቹ ወደ ማላዊ ይዞ ሲጓዝ የነበረው የጭነት መኪና ሾፌርም “ ማዕከላዊ ዶጎማ” ተብሎ በሚጠራው ከልል  ሲደርስ ችግር እንዳለ በመገንዘቡ  መኪናውን ለማቆም ይገደዳል።

ከዚያም  ስደተኞቹ ተጓዦችን ሲመለከት ከመካከላቸው 41  ሞተው መገኘታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤   አስከሬናቸውም በአካባቢው  በሚገኝ ጫካ ውስጥ መቀበሩን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በህይወት የተረፉት  ኢትዮጵያውያን ተጓዦች አደጋው በደረሰበት አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ከመካከላቸው አንዱ ዘግይቶ ማረፉን ሚኒስትር  ሲሊማ ጠቅሰዋል። ይህም የሟቾቹን ቁጥር ወደ 42 ከፍ አድርጎታል።

በህይወት የተረፉት ስደተኞች ጤናቸው ሲመለስ  ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡና  ከኤምባሲያቸው ጋር እንዲገናኙ እንደሚደረግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በተበላሸ ፖለቲካዊ አስተዳደር እና በኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ አገራቸውን ጥለው  በተለያዩ የ ዓለም ክፍሎች  የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  እየደረሰባቸው ያለው የከፋ  አደጋ  ብዙዎችን ያሳዘነ ሆኗል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide