ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2008)
ባለፈው ሳምንት የታንዛኒያ መንግስት በኬንያ ድንበር እንዲሰፍሩ ያደረጋቸው ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያና ስደተኞች ተመልሰው ወደታንዛኒያ እንደሚሄዱ የኬንያ ባለስልጣናት በድጋሚ ገለጡ።
ሁለቱ ሃገራት በኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ውዝግብ ውስጥ ቢሆኑም የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያውያኑ ጉዳይ መረጃ እንደሌለው አስታውቋል።
ይሁንና፣ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኖች ወደ ኬንያ ግዛት ዘልቀው እንዳይገቡ ጥበቃን እያደረጉ የሚገኙ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት 74ቱ ኢትዮጵያውያን ወደ ታንዛኒያ እንደሚመለሱ ዳግም ማረጋገጣቸውን ዘስታር የተሰኘ የኬንያ ጋዜጣ አስነብቧል።
የኬንያ የፀጥታ ሃይሎች በ74ቱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ባሉበት ወቅትም የኬንያ ፖሊስ በሳምንቱ መገባደጃ ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል የተባሉ ስድስት ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር የዋሉት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን የጉዞ መዳረሻቸው ታንዛኒያ እንደነበርም የኬንያ ፖሊስ ስደተኞቹን ዋቢ በማድረግ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ በድንበር አካባቢ ቁጥጥሯን ብታጠናክርም አሁንም ድረስ በየዕለቱ የሚሰደዱ መኖራቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት በመሸሽ ወደተለያዩ ሃገራት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ ከ70ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ጦርነት እልባት ወዳላገኘበት የመን መሰደዳቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ድርጊቱም አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ይገልጻል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች አዳዲስ የቁጥጥር ኬላዎችን በማቋቋም የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ጥረት ብታደርግም በርካታ ኢትዮጵያውያን ድንበርን በማቋረጥ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።