ከተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጋር ተያይዞ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌና የሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ደህንነት አደጋ ውስጥ እንደሆነ ተገለጸ

ኢሳት (ነሃሴ 4, 2008)

በኢትዮጵያ በመባባስ ላይ ያለው ህዝባዊ አመጽና የፖለቲካ አለመረጋጋት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ደህንነትን አደጋ ውስጥ እንደከተተው አንድ አለም አቀፍ የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ረቡዕ አስታወቀ።

የብሪታኒያ መንግስት በሃገሪቱ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ነውጥ ግምት ውስጥ በማስገባት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥረትን ማድረግ እንዳለበት ሪፕሪቭ የተሰኘው ተቋም ገልጿል።

በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሳምንቱ መገባደጃ ብቻ ወደ 100 የሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ያወሳው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፣ የብሪታኒያ መንግስት ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ትግል በማድረግ ላይ ባሉ አካላት ላይ የሚወስደው የሃይል ዕርምጃ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ዜጋውን እንዲታደግ ጥሪውን አቅርቧል።

በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ በመካሄድ ላይ ያለው ይኸው ህዝባዊ ተቃውሞ በተለያዩ ጊዜያት ለእስር ከተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች አሳሳቢ ስጋት እየሆነ መጥቷል ሲል የብሪታኒያው ድርጅት አመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ተቋምን ጨምሮ የብሪታኒያ የፓርላማ አባላትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች የብሪታኒያ መንግስት ዜጋውን ለማስፈታት ጠንካራ እርምጃን እንዲወስድ በማሳሰብ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በሪፕሪቭ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ውስጥ የሞት ቅጣት እንዲቀር አለም አቀፍ ቅስቀሳን በማድረግ የሚታወቁት ማያ ፎአ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ሰልፎች ላይ እየፈጸሙ ያለው ግድያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በሌሎች የፖለቲካ አመራሮች ላይ ተመሳሳይ እርምጃን ሊወስድ እንደሚችል ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ሪፖርቱን ረቡዕ ይፋ ያደርገው የብሪታኒያው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በሃገሪቱ በመባባስ ላይ ህዝባዊ አመጽ ለበርካታ ነዋሪዎችና ተማሪዎች እስርና ግድያ ምክንያት መሆኑንም አመልክቷል።

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩት የቀድሞ የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ባለፈው ወር በአዲሱ የሃገሪቱ የመንግስት ምስረታ የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ፊሊፕ ሃመንድ የኢትዮጵያ መንግስት በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ ግልፅነትን እንዲያሳይ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ባለስልጣኑ በሃገሪቱ ያደርጉትን ጉብኝንት ተከትሎ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የህግ የምክር አገልግሎት አያስፈልጋቸውም ሲል የያዘውን አቋም በመቀየር የህግ አካላት አቶ አንዳርጋቸውን እንዲጎበኙና የህግ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ስምምነት መፈጸሙም የሚታወቅ ነው።