ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2008)
ከአዲስ አበባም ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱንና በክልሉ ፍርሃት ነግሶ መገኘቱን የፈረሳይው ፍራንስ 24 የቴለቪዥን ጣቢያ ማክሰኞ ዘገበ።
ከቴለቪዥን ጣቢያው ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረጉት የጊንጪ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው አሁንም ድረስ በአካባቢው እስራት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
የገቡበት ያልታወቀ ነዋሪዎች መሆናቸውን ያስረዱት ነዋሪዎቹ የጸጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃ ሲወስዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ወርቁ ባዩ የተባሉና በተቃውሞው አስቻለው የተባለ ልጃቸው እንደተገደለባቸው የገለጹት የአካባቢው አርሶ አደር፣ ነዋሪዎች መሬታቸው እየተወሰደ ለባለሃብቶች መሰጠቱን በመቃወም ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸውን ለቴሌቪዥን ጣቢያው አስረድተዋል።
መሬታቸን ተወስዶብን በምትኩ የሚሰጠን ገንዘብ በቂ አይደለም ሲሉ ያስታወቁት አርሶ አደሩ መሬታቸውን በማጣታቸው ምክንያት ኑሮአቸው ክፉኛ መጎዳቱን ገልጸዋል።
ሶስተኛ ወሩን የዘለቀው ይኸው የክልሉ ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ጋር በዘለለ የእኩልነት መብትና የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ ያካተተ እንደሆነ ፍራንስ 24 በዘገባው አስፍሯል።
ግርማ ቱራ የተባለ የከተማዋ ነዋሪ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አሁንም ድረስ ማስፈራራትን እያካሄዱ እንደሆነና በየቦታው አስከሬኖች በመገኘት ላይ መሆናቸውን ለቴሌቪዥን ጣቢያው አስረድተዋል።
በክልሉ ተቀስቅሶ ባለው በዚሁ ተቃውሞ ከ200 የሚበልጡ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩም ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።