ሐምሌ ፳፫(ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጣና ሞባይል የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ደንበኛ ከሆነው ከቻይናው ግዙፍ ቴሌኮም ኩባንያ ዜድ.ቲ.ኢ ጋር በጋራ ለመስራት በደረሱት ስምምነት መሰረት በ2003 ዓ.ም በ50 ሚሊየን ብር ወጪ በባህርዳር ከተማ ዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎችን ማምረቻ ፋብሪካ በመክፈት ምርቱን ለአገር ውስጥ ገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
ሆኖም ፋብሪካው ባልታወቀ ሁኔታ ከቀጠራቸው ሠራተኞቹ መካከል ወደ 70 የሚጠጉትን ከዚህ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በይፋ ማሰናበቱን ምንጮቻችን ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያው በተለይ አርሶአደሩ በዝቅተኛ ገንዘብ የሞባይል ቀፎ ከቀረበለት ይገዛል በሚል ስሌት የተመሰረተ ቢሆንም ከተቀናቃኝ ወገኖች ኩባንያው የኢህአዴግ ንብረት መሆኑንና ሞባይሉም ድምጽ እየቀዳ ለደህንነት መ/ቤት ያስተላልፋል የሚል ወሬ በመነዛቱ አርሶአደሩ በግዳጅ ጭምር ለመግዛት የሚደረገውን ጉትጎታ እምቢ ማለቱን ተከትሎ ገበያው ማሽቆልቆሉ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጫችን ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ከሚገጣጠሙ የሞባይል ቀፎዎች የቻይናዎቹ ቴክኖ እና ስማድል ሞባይል መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ገበያውን በከፍተኛ ደረጃ መቆጣጠራቸው ለኢህአዴጉ ኩባንያ ኪሳራ ተጨማሪ መንስኤ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ሰኔ 20 ቀን 2005 በድንገት በተለጠፈ ማስታወቂያ ከስራ መሰናበታቸው የተነገራቸው ሰራተኞች እስካሁን ጥቅማጥቅማቸው እንዳልተከበረላቸው ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
አብዛኞቹ የተቀነሱት ሰራተኞች የብአዴን አባላትና ደጋፊዎች ናቸው።