ኢሳት (ሰኔ 16 ፥ 2008)
በተያዘው የኢትዮጵያ 2008 በጀት አመት ከአለም አቀፍ የቡና ንግድ ሊገኝ የታሰበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ140 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ አስመዘገበ።
በተያዘው የፈረንጆች አመት በአለም አቀፍ ደረጃ የታየው የቡና ዋጋ መቀነስ የኢትዮጵያ የቡና ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳሰሩን የንግድ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የታየውን የዋጋ መቀነስ ተከትሎ በቡና ንግድ ላይ የተሰማሩ በርካታ ድርጅትች ቡናን ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይሁንና የንግድ ሚኒስቴር ሁሉም ቡና ላኪ ኩባንያዎች ቡናን በተገኘው ዋጋ ለአለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው አዲስ መመሪያን ተግባራዊ ያደረጉ ሲሆን፣ መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ተወስኗል።
የንግድ ሚኒስቴር ከቡና ንግድ የሚገኘው ገቢ ማሽቆልቆልን እንዳያሳይ በማሰብ አዲሱን መመሪያ በስራ ላይ ቢያውልም ከቡና ንግድ የተገኘው ገቢ ባለፉት 10 ወራቶች ብቻ በ146 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ለሃገሪቱ በዋነኝነት የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኘው የቡና ገቢ መቀነስ በውጭ ምንዛሪ ክምችትና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር ተገልጿል።
በንግድ ሚኒስቴር የቡና ገበያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌታሁን ቢኮራ የታየውን የገቢ ማሽቆልቆል ለማካካስ በቀጣዮቹ ወራቶች ርብርብ እንደሚደረግ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በተያዘው 2016 የፈረንጆች አመት ኢትዮጵያ 230 ሺ ቶን ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት እቅድ መያዙን ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና የብራዚል መንግስት የሃገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሆነው የብራዚሊያን ሪል ከዶላር ጋር ያለው ምንዛሬ እንዲቀንስ በማድረጉ ምክንያት የአለም ቡና ዋጋ ቅናሽ ማሳየቱ ታውቋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዓለም ገበያ ቡናን የሚያቅርቡ ሃገራት ብራዚል በወሰደችው እርምጃ ክፉኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአለም የፋይናንስ የንግድ ተቋማት መረጃዎች ያመልክታሉ።