ከቆሼ አደጋ የተረፉ ነዋሪዎች ህጋዊ አይደላችሁም ተብለው ከጊዜያዊ መጠለያ እንዲወጡ መደረጋቸውን አስታወቁ

ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2009)

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ አደጋ የተረፉና በጊዜያዊ መጠለያ እንዲቆዩ የተደረጉ ነዋሪዎች ህጋዊ ነዋሪዎች አይደላችሁም ተብለው ከመጠለያ እንዲወጡ መደረጋቸውን አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ የተደርጉ ሰዎች በአደጋው ተጎጂ እንደነበሩና እንዳልነበሩ የመለየት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ሃሙስ ገልጿል።

ይሁንና በጊዜያዊ መጠለያው የሚገኙ በርካታ ሰዎች ከአደጋው ተርፈው በመጠለያ እንዲገቡ ቢደረግም ሰሞኑን በተጀመረው የመለየት ስራ ህጋዊ ነዋሪና ተጎጂ አይደላችሁም ተብለው ከመጠለያ እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ አበባ እሸቱ በበኩላቸው ተጎጂ የሆኑ ነዋሪዎችን የመለየት ስራው በፎቶና በተለያዩ መንገዶች ማጣራት እየተካሄደበት እንደሆነ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ምላሹን ሰጥተዋል።

በአካባቢው የደረሰውን አደጋ ተከትሎ 113 ሰዎች መሞታቸውን መንግስት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር ከአደጋው የተረፉ ሰዎች በጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ በማድረግ ዘላቂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ቃል መግባቱ ይታወሳል።

በመጠለያው ገብተው አስተዳደሩ እያካሄደ ባለው የማጣራት ስራ እንዲወጡ የተደረጉ ነዋሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ ለችግር መጋለጣቸውንና እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ሳምንት የአካባቢው ነዋሪዎች ዳግም አደጋ ሊደርስ ይችላል ተብለን ያለምንም አማራጭ ስፍራውን እንድንለቅ ተደርገናል ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው አይዘነጋም።

የክልል መንግስታችንን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ባለሃብቶች ከአደጋው ለተረፉ ሰዎች ድጋፍ ይሆን ዘንድ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሳቸው ታውቋል።

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞቹ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማቋቋም ይረዳ ዘንድ በስልክ ከሶስት ብር ጀምሮ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዘመቻን እያካሄደ ይገኛል።