(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2010)የኢትዮጵያ መንግስት ከሱማሌላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ማድረጉን የሶማሊያ ፓርላማ ውድቅ አደረገ።
እርምጃው ሉአላዊነትን መድፈር ነው ሲል ፓርላማው አውግዟል።
ዲፒ ወርልድ ወይንም ዱባይ ፖርት የተባለው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ኩባንያና የኢትዮጵያ መንግስት የበርበራ ወደብን ድርሻ በመውሰድ ለመጠቀም ከሱማሌላንድ መንግስት ጋር ያደረጉትን ስምምነት የሱማሊያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውድቅ አድርጎታል።
170 አባላት ካሉት የምክርቤት አባላት ውስጥ 168 የሚሆኑት ናቸው ውድቅ ያደረጉት።
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውሳኔ በሴኔቱ ሲፀቅ በፕሬዝዳንቱ ፊርማ ህግ እንደሚሆን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
ከወዲሁ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላ ፎርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ ሐሰን ዲፒ ወርልድና የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሌላንድ ጋር ያደረጉት ስምምነት አለም አቀፍ ህጎችን ከመፃረሩም በላይ የአንድ አገርን ሉአላዊነት መድፈር እንደሆነ ተናግረዋል።
የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢ ሃብዲ የሶማሊያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስምምነቱን አለመቀበሉ ጦርነት እንደማወጅ አድርገው እንደሚወስዱት ገልፀዋል።
ሶማሌላንድ ራሷን እንደ አገር የመሰረተች የራሱ መገበያያ ገንዝብ ያላትና አለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና እንዲሰጣት ጥያቄ ማቅረቧን ፕሬዝዳንቱ አክለው ተናግረዋል።
እንደ አፍርካ ኒውስ ዘገባ ከሆነ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ 19 በመቶውን ድርሻ ስትወስድ ዲፒ ወርልድ 51 በመቶውን ይይዛል። ቀሪው 30 በመቶ በሶማሌላንድ እጅ የሚቀጥል ይሆናል።