ኢሳት (ግንቦት 17 ፥ 2008)
በመሰረታዊ ብረታብረት ኮርፖሬሽንና በስኳር ኮርፖሬሽን መካከል ከተፈጠረው ውዝግብ ጋር በተያያዘ በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ነባር ታጋዮች በሰራዊት አዛዦች መካከል ፍጥጫ መቀጠሉ ተሰማ። የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች ሪፖርቱን በፓርላማ እንዲያቀርቡ ድጋፍ ያደረጉትና ማበረታቻ የሰጡት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ከ6 ዓመታት በፊት ከመንግስት በተመደበለት በ10 ቢሊዮን ብር ካፒታል ስራውን የጀመረው የመሰረታዊ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር ብድር ለተጠየቀበት የስኳር ፋብሪካዎች ውድቀት ተጠያቂ መሆኑ በፓርላማው ከመገለጹ ባሻገር፣ በርካታ ፕሮጄክቶችን በማጓተት እና ከሰራው በላይ ገንዘብ ቅድሚያ በመወሰድ እንዲሁ በአቅም ማነስ እየተወቀሰ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ስርዓቱ ውስጥ ለተፈጠረው ልዩነት የፍልሚያ ሜዳ እየሆነ መምጣቱ የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።
በመቀሌ በተካሄደው የህወሃት ጉባዔ ወደ ፓርቲ አመራር ይመለሳሉ ተብለው የተጠበቁትና በተራ አባልነታቸው ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ የተደረጉት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ወደ አመራር ላለመመለሳቸው የመከላከያ የጦር አዛዦችን በተለይም ጄኔራል ሳሞራ የኑስን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ የሚገልጹት ምንጮች፣ ጄኔራል ሳሞራና ዶ/ር አርከበ ሰላምታ እንኳን የማይለዋወጡበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ያስረዳሉ።
በቀድሞ የህወሃት ታጋይ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ጄኔራል ሳሞራ የኑስን ጨምሮ የተወሰኑ የቀድሞ የህወሃት ታጋይ የነበሩ ጄኔራሎች በቅርብ የሚሳተፉበትና የሚቆጣጠሩት ተቋም ከየአቅጣጫው የሚነሳበትን ወቀሳ ተከትሎ አቶ አርከበ እቁባይ በዚህ የብረታብረት ኮርፖሬሽን ላይ ምርመራ እንዲያካሄድና ለዚህም ግብረሃይል እንዲቋቋም ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት በአቶ ሃይለማሪያም ፊርማ የተመሰረተው ግብረ ሃይል ለሁለት ወራት ጥናቱን ስያካሄድ ቆይቷል። በጥናቱ ማጠቃለያም ከብረታብረት ኮርፖሬሽን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያይል ይፍረስ የሚል የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል፣ ግብረ ሃይሉ ኮርፖሬሽኑ ይፍረስ የሚለውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ዶር አርከበ ግፊት ማድረጋቸውም ተመልክቷል።
የኢሳት ምንጮች እንደሚገልጹት የግብረሃይልን የውሳኔ ሃሳብ በሌላ ተጨማሪ ሁኔታ ለማጠናከር የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች ከሜቴክ ጋር ያላቸውን ውልና አፈጻጸም በተመለከተ ሪፖርት እንዲያዘጋጅ መመሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ አዲሱ ስራ አስኪያጅ ስለጉዳዩ የተሟላ መረጃ የላቸውም በሚል ከአቶ ሃለማሪያም ጋር በስጋ የሚዛመድና በኮርፖሬሽኑ ውስጥ የሚሰሩ ሰው ሪፖርቱን እንዲያዘጋጁት መደረጉ ተዘርዝሯል።
የተዘጋጀውን ሪፖርት በማየት የውሳኔ ሃሳብ ነጥቦችን በማካተት ዶ/ር አርከበ አስተዋጽዖ አድርገዋል። ከዚያም የኮሮፖሬሽኑ ሃላፊዎች በፓርላማ የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን ግንቦት 1 ቀን 2007 ባቀረበበት ወቅት “ለስኳር ኮርፖሬሽኖች መውደቅ ሜቴክ ከፍተኛ ድርጃ አለው” በማለት በፓርላማውም ከመናገራቸው በተጨማሪ፣ “የቀድሞ የስኳር ኮሮፖሬሽን ሃላፊዎች መጠየቅ አለባቸው።” ሲሉ ያልተጠበቀ ሪፖርት አቅርበዋል።
የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በቃሉ መሰረት አለመገኘቱን ይልቁንም ሳይሰራ ገንዘቡን በአብዛኛው መሰብሰቡን ኣጋልጠዋል። የስኳር ኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች ያቀረቡት ሪፖርት ዕውነት የተመረኮዘ ቢሆንም፣ ማሳሰቢያውና ምሬቱ በእነ ዶ/ር አርከበ የተቃኘ ስለመሆኑ ከኢሳት ምንጮች ለመረዳት ተችሏል።
ይህንን ሪፖርት ተከትሎ ሜቴክ ይፍረስ የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ በእነ አርከበ ዕቁባይ በኩል ጥረቶች ሲቀጥሉ፣ ጄኔራል ሳሞራን ጨምሮ የተወሰኑ ጄኔራል መኮንኖች በሁኔታው መቆጣታቸው ተሰምቷል። የመዝገቡ ወይንም የፍጥጫው ፍጻሜ ሳይለይ ቀጥሏል።
የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስኳር ኮሮፖሬሽኖች ላይ ላደረሰው ውድቀት የሜቴክ ሃላፊዎችና አቶ አባይ ጸሃዬ ዋነኛ ጠተያቄ መሆናቸው ቢገለጽም፣ የቦርድ ሊቀመንበሩና አባላቱ ከደሙ ንጹህ አይደሉም የሚሉ ተቃውሞዎች እየተሰሙ ይገኛሉ።
የስኳር ኮርፖሬሽን የቦርድ ሊቀመንበር የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የትግራይና የአፋር ክልሎች ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የጠ/ሚኒስትሩ የጸጥታ አማካሪ አቶ ጸጋይ በርኸ የቦርድ አባላት ቢሆኑም በተለይ ባለፉት 3 ዓመታት ዝምታን መምረጣቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል የሚል ተቃውሞ እየተሰማ ነው።
አቶ አባይ ጸሃዬ የመንግስት የፋይናንስ ስርዓት በተላለፈ መንገድ ከሚፈጽሙት ባሻገር፣ የሚጠረጥሯቸውን የፋይናንስ ሃላፊዎችና ሌሎችን ያለተጨባጭ ምክንያት ሲያባርሩ ቦርዱ ዝምታን መርጧል ሲልም ተቃውሞ ቀርቧል። በሌላ ወገን የቦርዱ ሊቀመንገር አቶ አህመድ አብተው በስኳር ኮርፖሬሽን ላይ ጠቅላይ ኦዲተር ምርመራን እንዲያካሄድ ለአቶ ሃይለማሪያም አምና በደብዳቤ ጠይቀው ምላሽ ማጣታቸውን ተሰምቷል።
አቶ አባይ ጸሃዬ በኢትዮጵያ የንግድ ባንክ ውስጥ ባላቸው ተፅዕኖ የማድረግ አቅም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአቅሙ በላይ ለስኳር ኮርሬሽኑ ብድር እንዲሰጥ ሲያደርጉ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ተባባሪ ሆነው መገኘታቸው በዚህም ከዚሁ ባንክ ብቻ 47 ቢሊዮን ብር በብድር መውጣቱ ታውቋል። የባንኩ ፕሬዚዳንት አሁን ከአቶ አባይ ጸሃዬ ተፅዕኖ ስር ወጥተው ወደ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ተፅዕኖ ስር በመግባታቸው የስኳር ኮርፖሬሽኖቹ ዕዳውን በ20 ዓመታት አይመልሱትም የሚል መግልጫ መስጠታቸው በኢሳት ምንጮች ተዘርዝሯል።
መሰረታዊ የብረታብረትና ኢንጂነሪን ኮርፖሬሽን የፌዴራል መንግስት ንብረቶችን ለጥገና ወስዶ፣ ለትግራይ ክልል በመስጠትና ትልልቅ ፕሮጄክቶችን በመቀሌ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች በመዘርጋት እያከናወነ ያለው ስራ፣ የህወሃት አመራሮችን ያስማማ ነጥብ ቢመስልም፣ በእነ ዶ/ር አርከበ የሚዘረፈው ይበልጣል የሚለውን ምክንያት ጨምረው ከጄኔራሎቹ ጋር ፍጥጫው ቀጥለዋል።