ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)
መንግስት ከሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ርክክብ ጋር በተገኛኘ ከደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ በተጨማሪ ለግል ባለሃብቶች ከተሸጡ የልማት ድርጅቶች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰቡን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ለመንግስት ገቢ ማድረግ የነበረባቸውን ክፍያ ያልፈጸሙት ድርጅቶች 28 ሲሆኑ 60 በመቶ የሚሆነው እዳ በሚድሮክ ኩባንያ ያልተከፈለ ገንዘብ መሆኑም ተገልጿል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶቹን የተረከቡት ባለሃብቶች በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ክፍያን ለመጨረስ ስምምነት ቢያደርጉም የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ሳይወጡ መቅረታቸውን የሚኒስቴሩ ሃላፊዎች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ውዝፍ እዳ ያለባቸውን እነዚሁን 28 የግል ድርጅቶች ለህግ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አክሎ ገልጿል።
የልማት ድርጅቶቹን የተረከቡት 28ቱ የግል ኩባንያዎች በመብራት መቆራረጥ፣ በጥሬ ግብዓት እጥረትና በተያያዥ ጉዳዮች ሳቢያ ስራቸውን ሊያከናውኑ እንዳልቻሉና እዳቸው መክፈል ሳይችሉ መቅረታቸውን አስታውቀዋል።
ይሁንና፣ የሚንስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወንደፍራሽ አሰፋ ኩባንያዎቹ ያቀረቡት ምክንያት አጥጋቢ አይደለም በማለት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶቹን የተረከቡት ክባንያዎች 35 በመቶ ቅድመ ክፍያን በመፈጸም ቀሪውን 65 በመቶ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል መግባታቸው ታውቋል።
ከ2.1 ቢሊዮን ብር እዳ ውስጥ 60 በመቶ ድርሻን ይዟል የተባለው ሚድሮክ ኩባንያ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ አለመስጠቱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያን ልማት ባንክ ከሰፋፊ የእርሻ መሬት ርክክብ ጋር በተገናኘ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ያበደረው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የገባበት እንደማይታወቅ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኪሳራን አስከትሏል የተባለውን ጉዳይ ለማጥናትም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ትዕዛዝ አንድ ብሄራዊ ቡድን ተቋቁሞ ጉዳዩን እየመረመረ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወቃል።
ይህንኑ ኪሳራ ተከትሎም መንግስት የሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ርክክብን ያቆመ ሲሆን የልማት ባንክም ለዘርፉ የሚሰጠው ብድር እንዳቆመ ይፋ አድርጓል።