ሚያዚያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ቢቢሲ የአለም ባንክን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች በመጪዎቹ ሶስት አመታት ከሌላው አለም አማካኝ የእድገት መጠን ጋር ሲተያይ የተሻለ እድገት ያሳያሉ።
የአብዛኞቹ አገራት እድገት ጥሬ እቃዎችን ወደ ውጭ አገራት በመላክ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያመለከተው ዘገባው፣ የስራ አጥ ቁጥር መጨመር እና ከጥሬ እቃዎች ባሻገር ገቢን ለመጨመር የሚያስቸሉ ሌሎች የስራ መስኮች ባለመፈጠራቸው በእድገቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያስከትል ይችላል።
የአፍሪካ መንግስታት ከጥሬ እቃዎች ሽያጭ የሚገኘው ሀብት ለህዝቡ ልማት መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው ባንኩ አሳስቦአል።
አፍሪካዊያን በመንገዶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ በበቂ ሁኔታ መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ባንኩ ምክሩን ለግሷል።
የአፍሪካ ጥሬ ሀብት ሽያጭ መጨመር በአብዛኛው ከቻይና ፈጣን እድገት ጋር የተያያዘ መሆኑ በዘገባው ተመልክቷል።