ከሦስት ወረዳዎች 10 ሺህ ገበሬዎች ሊፈናቀሉ ነው የአካባቢው ባለስልጣን “የሚፈናቀል የለም” እያሉ ነው።

ሐምሌ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ከአርሲ ዞን ሦስት ወረዳዎች ብቻ ከ 10፣000 በላይ  ገበሬዎች “ቦታችሁ ለልማት ይፈለጋል” ተብለው ከይዞታቸው በግዳጅ ሊፈናቀሉ መሆናቸው ተሰማ።

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከምዕራብ አርሲ ዞን ሶስት ወረዳዎች የተወከልን ነን የሚሉ ገበሬዎች ፦”ከሥራችንና ከመኖሪያችን እንድንነሳ  ማስጠንቀቂያ እየተሰጠን ስለሆነ፤ ፍትህ ይሰጠን” ሲሉ አቤት በማለት ላይ መሆናቸውን ፍኖተ ነፃነት ዘግቧል።

‹‹ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ ተይዞ የነበረውን ቀያችንን ‹ልቀቁና ሂዱ!› በመባላችን እጅግ አዝነናል›› ያሉት ገበሬዎቹ ፤ በመፈናቀሉ ሂደት ከሦስቱ ወረዳዎች ከ10 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ሊነሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ገበሬዎቹ የሚፈናቀሉትም፤ከአርሲ ነጌሌ፣ከጂዳ አዳሚቱሉ እና ከአናሻላ ወረዳዎች እንደሆነ ወኪሎቹ አመልክተዋል።

ከ40በላይ የሚሆኑ የገበሬዎች ተወካዮች እንደሚናገሩት ፤የእርሻ መሬታቸውን፣ ከብቶቻቸው የሚውሉበትንና የመኖሪያ ቀያቸውን ሳይቀር ‹ልቀቁ› ተብለዋል።

“ከዚሁ ጋር በተያያዘ በየቀበሌውና በየወረዳው የተመደቡ ካድሬዎች የዜግነት መብታችንን እየገፈፉን ናቸው”ያሉት ተወካዮቹ፤በየወረዳውና በዞናችን ላሉ ኃላፊዎች ብናመለክትም፤ እንኳን መፍትሔ ልናገኝ ፤ በአግባቡ እንኳን ሊያናግሩን ፈቃደኞች አልሆኑም”ብለዋል።

በአካባቢያቸው ሹመኞች መፍትሔ ሲያጡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት  ለኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት አቤት ለማለት መገደዳቸውን የተናገሩት ገበሬዎቹ፤የሚመለከታቸው የክልሉ ተወካዮችም ጉዳዩን ተመልክተው ውሳኔ ለመስጠት ለትናንት ሐምሌ 18 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ እንደሰጧቸው ገልፀዋል፡፡

ተወካዮቹ ወደ ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በመሄድም፦‹‹ የአካባቢያችን ሹመኞች ህዝብን ከመኖሪያና ከሥራ ቦታ እያባረሩ ‹ለህዝብ ነው፤ ለልማት ነው› እያሉ በህዝብ እየቀለዱ ነው፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው የመንግስት አካል ጉዳዩን በጥሞና ተመልክቶ ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጠን ጩኸታችንን አሰሙልን፡፡›› ሲሉ አቤት ብለዋል።

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የምዕራብ አርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ገ/መድኅን  ግን”ከወረዳዎቹ የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች የሉም” ነው የሚሉት።

የተጠቀሱት አካባቢዎች ለረዥም ጊዜ  በአቢያታና ሻላ ሐይቆች ዙሪያና  በብሔራዊ ፓርኩ ክልል ውስጥ የኖሩ በመሆናቸው ፓርኩ ላይ  የዳግም ከለላ እየተደረገ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ተሰማ፤ በጉዳዩ ዙሪያም የአካባቢው ነዋሪዎችና ሽማግሌዎች፣ ከሚመለከተው የመንግስት አካላት ጋር ተወያይተው የመፍትሄ አቅጣጫ መያዙን አስታውሰዋል፡፡

በውይይቱ ሦሥት አማራጮች ቀርበው በሁለተኛው አማራጭ ላይ ከስምምነት መደረሱን ያመለከቱት አቶ ተሰማ፤ በዚህም መሰረት ፤ነዋሪዎቹ ቀደም ሲሉ የሰፈሩ ከመሆኑ አንፃር ፤ፓርኩን በማጥበብና ነዋሪውን ከፓርኩ ክልል ውጭ በማድረግ ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለመስጠት መታሰቡን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ጉዳዩ ገና  እስካሁን እልባት ያላገኘ መሆኑን  አቶ ተሰማ አልሰሸጉም።

____________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide